ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተላለፈ የሐዘን መግለጫ

እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን በመጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም በተከሰተው አሰቃቂ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ምክንያት የበርካታ ወገኖቻችን ሕይወት ማለፍ እና ብዙ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አይተን በእጅጉ አዝነናል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሶዶ ሀገረስብከት፣ እና የጳጳሳት ጉባኤ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦታው በመገኘት ቤተክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ መጀምሯን እንገልጻለን። ሆኖም ግን ከአደጋው አስከፊነት አንጻር የመላው ኢትዮጵያውያን እና በጎ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ሰብዓዊ ድጋፍ አስፈላጊ ነውና በአፋጣኝ እንዲረባረቡ እንጠይቃለን። “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” (ሮሜ 12፥15) ብሎ በሚያስተምረን የእግዚአብሔር ቃል ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ከወገኖቻችን ጎን እንቁም!
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገለጸው ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ የሐዘን ጊዜ ከወገኖቻችን ጋር በአንድነት በመስዋዕተ ቅዳሴ እንድንጸልይ እና ለተጎጂዎች የሚገባውን የሰብአዊ ድጋፍ በፍጥነት እንድናደርግ መንፈሳዊ ጥሪ እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ለመላው ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን። ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ ይቀበላቸው፤ ዘለዓለማዊ እረፍትን ይስጣቸው፤ ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸውም እውነተኛ መጽናናትን ፈጣሪ ይስጥልን።
ቸሩ መድኃኔዓለም ሀገራችንን ይጠብቅልን!
