የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ሐዋርያዊ መልዕክት

“ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን” (ዮሐ 20፡19)
ለክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣
ለመላው ካቶሊካውያን ምዕመናን እና በጎ ፍቃድ ላላችሁ ሰዎች ሁሉ
ኢትዮጵያውያን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ሐዋርያቱን ሰላም ባለበት ክርስቲያናዊ ሰላምታ “ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን” እንላለን። እነዚህ ቃላት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 14ኛ በእረኝነት በተመረጡበት ዕለት መላው የዓለም ህዝብን ሰላም ለማለት የተጠቀሙት ሲሆን በዕለት ተዕለት የሥርዓተ አምልኳችን ካህናት “ሰላም ለኵልክሙ” በማለት እንጠቀማቸዋለን።
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት 58ኛ መደበኛ ጉባኤያችንን ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ሞጆ በሚገኘው የኮንሶላታ አባቶች ገዳም እያደረግን ባለንበት ጊዜ “ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን” እንላለን። በጉባኤያችን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያናችን ተልዕኮ፣ ስላሏት መልካም ዕድሎች እና ተግዳሮቶቿ ስንወያይ ቆይተናል። ባደረግነውም ጥልቅ ውይይት እና አስተንትኖ በጉባኤያችን ማጠቃለያ ለመላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ እምነታችሁን በተስፋ፣ በሰላም እና በደስታ ትኖሩ ዘንድ ይህን ሐዋርያዊ መልዕክት ለማስተላለፍ ወደናል።
እግዚአብሔር አምላክ ስለመልካምነቱ እና ለተልዕኳችን በሚያስፈልገን ጸጋ ስለባረከን እንዲሁም ቁርጥ ፍቃድ ያላቸው በርካታ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ካቲኪስቶች፣ ምዕመናን እና ሌሎች በጎ ፍቃድ ያላቸው አገልጋዮችን ስለሰጠን እናመሰግነዋለን። በሲኖዶሳዊ አብሮ የመጓዝ መንፈስ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ራሳችሁን በማደስ የአንዲት ቤተክርስቲያን ተልዕኮ ለሆነው ወንጌልን ለመስበክ ስላላችሁ መልካም ፈቃድ እና በጸጋው በተሞላው አገልግሎታችሁ እጅግ ደስተኞች ነን። በአገልግሎታችሁ በሁሉም ዕድሜ ለሚገኙ የሚገኙ ምዕመናንን በቤተሰብ ህይወት እና በጥሪ ህይወትን በማበረታታት ዘላቂ ዕቅዶች ላይ በማተኮር የእምነት ህንጸት አተምህሮዎችን ቅድሚያ እንድትሰጡ አደራ እንላለን። በቤተክርስቲያናችን የ10 ዓመት ዕቅድ እንደተገለጸው ቁምስናዎቻችን የስብከተ ወንጌል ማዕከል በማድረግ የተጠመቁ ሁሉ የስብከተ ወንጌል አቅማቸውን ከምንግዜውም በላይ የሚያጎለብቱበት እና ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ አስተዋጾ የሚያደርጉበት አማራጮች እንዲያመቻቹ እናሳስባለን።
ቤተክርስቲያናችን ላለፉት 3 አመታት ያህል ዝግጅት በማደረግ ይፋ ያደረግችው የመጨረሻው “አብሮ መጓዝ” የሲኖዶስ የትግበራ ሰነድን ሁላችሁም በጽሞና እንድታነቡትና በሥራ ላይ እንድታውሉት እናበረታታለን። ይህ ሰነድ ሁሉም ቁምስናዎች በሐዋርያዊ ተልዕኮዎቻቸው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት፣ በተሳትፎ፣ በሲኖዶሳዊ መንፈስ እንዲለማማዱ የሚያግዝ መሆኑን እንገልጻለን። በዚህ እየተገበራችሁ ባላችሁት ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎት እኛ እረኞቻችሁ በቅርበት ከእናተ ጋር አብረናችሁ መሆናችንን ልናረጋግጥ እንወዳለን።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እህቶች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ፥ አሁን በሀገራችን በምንሰማው እና በምናየው የግጭት እና ያለመረጋጋት ሁኔታ እጅግ እናዝናለን። በአጠቃላይ በአለማችን እና በሀገራችን በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶች እንዳሉ እንመለከታለን። ካለፈው የጦርነት ህመማችን ሳናገግም በዚህ ወቅት በየቦታው ያሉ ግጭቶች የበርካታ ንጹሃንን ህይወት እየቀጠፉ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እያፈናቀሉ፣ ንብረትን እና ተፈጥሮንም እያወደሙ ይገኛሉ።
ስለዚህ አሁንም በተስፋ በተሞላ ልብ “ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን” እንላለን! እንደሀይማኖት አባቶች እና መሪዎች፣ በሀገራችን ያለው የሰላም ዕጦት ያሳስበናል። ስለዚህም አሁንም ስለሰላም እንድንጸልይ እና እንድንሰራ ለሚመለከታችሁ ሁሉ ጥሪ እናደርጋለን። እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት በድጋሚ መላው ካቶሊካውያን ምዕመናን እና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን እና ሰላም ወዳድ የሆናችሁ ሁሉ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድ እንድንጾም፣ እንድንጸልይ፣ እና ለሰላም እንድንተጋ እንማጸናለን።
- ስለሰላም እንጸልይ
እ.አ.አ ባሳለፍነው የጥር ወር 2025 ዓ.ም በተከበረው የአለም አቀፍ የሰላም ቀን የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነፍስኄር ፍራንቼስኮስ እንዲህ ሲሉ ጸልየዋል። “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰላምህን ስጠን፣ በዚህ ከፊታችን ለሚመጣው አዲስ ዓመት ለሀገር መሪዎች እና ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ለአለም አቀፍ ድርጅት መሪዎች እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ በማስተላልፈው መልካም ምኞት መልዕክት ጸሎቴ ይኸው ነው። ጌታ ሆይ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በልልን። በዚህ የይቅርታ መንገድ ውስጥ አንተ ብቻ የምሰጠንን እውነተኛ ሰላምህን ስጠን። ሁላችንም በግል እና በማህበራዊ ህይወታችን በቁርጠኝነት እውነተኛ ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ስለሆነ እና እንደሆነም ስለምናምን ለሀገራችን ብሎም ለመላው አለም ስለሰላም ስጦታ ሁላችንም እንድንፀልይ እንጠይቃለን። ይህ ሁላችንም የሰው ልጅን ክብርና መብት እንድንጠብቅ ለእያንዳንዳችን የተሰጠን ጥሪ እና ኃላፊነት ነው። ስለሆነም እያንዳንዳችን በግላዊም ሆነ ማህበራዊ ጸሎታችን፣ በሥርዓተ አምልኳችን፣ የእግዚአብሔር ምህረት እና ይቅርታ እንድንለምን፣ እና እርስ በእርሳችን ይቅር የምንባባልበትን ጸጋ እንዲሰጠን እንድትጸልዩ እናሳስባለን። በተጨማሪም ለፖለቲካዊም ሆነ ለማህበራዊ ችግሮቻችን የምንሰጣቸው መፍትሔዎቻችን በትዕግስት፣ በብልሃት እና ፈሪሃ እግዚአብሔር በተሞላበት መንፈስ በጠረጴዛ ዙሪያ የተወያየንባቸው እንጂ በጦርነት ወይም በግጭት የሚፈቱ መሆን እንደሌለባቸው እናሳስባለን። የመንግስት እና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን የምትመሩ፣ በኃላፊነት ቦታ ላይ የምትገኙ ሰዎች አቅማችሁን እና ጥበባችሁን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ ለዕርቅ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ታዉሉት ዘንድ እንጸልያለን። በአለማችን በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሰላም እጦት እና ጦርነት እንዲቆም፣ በአንፃሩ እውነተኛ ሰላም ይሰፍን ዘንድ እንጸልያለን።
2. ስለሰላም እንጹም
“ጾምን፤ አምላካችንን ስለዚህ ነገር ለመንን፤ እርሱም ልመናችንን ሰማ” (መ. ዕዝራ 8፡23) በበርካታ የሀይማኖት ሥርዓቶች መሰረት ጾም ራስን ከኃጢአት ለመግታት፣ ለሰላምና ለፍትህ ለመቆም እንደሚረዳ ያስተምራሉ። በዚህ ወቅት በርካታ ወንድሞቻችና እህቶቻችን በጦርነት እና በግጭት ምክንያት በምግብ እጦት እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ስለሆነም የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆናችሁ ሁላችሁ ስለሰላም ብላችሁ በጦርነት እና በስቃይ ላይ ካሉ ወገኖቻችን ጋር በህብረት በመቆም ለሀገራችን፣ ለጎረቤት ሀገራት፣ እንዲሁም ለመላው ዓለም እንድትጸልዩ እንማጸናለን። መላው የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በዕለት ተዕለት ግላዊም ሆነ ማህበራዊ ህይወታችሁ ጾምን እንድትለማመዱ እና በወንድማማችነት መንፈስ መኖር እንድንችል እንድትጸልዩ ጥሪ እናቀርባለን። ይህንንም በምናረግበት ወቅት ከምግብ ብቻ ራሳችንን በመቆጠብ ብቻ ሳይሆን ጾማችንንም ሆነ ጽሎታችንን ከሚመርዙ እና ግጭትን ከሚያነሳሱ ከሃሜት፣ በግልም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግር በመቆጠብ ሊሆን ይገባል። ግጭትን ከሚያነሳሱ እና ጥላቻን ከሚዘሩ ውይይቶች መራቅ ወይም አለመሳተፍ ያስፈልጋል። ከፊታችን በሚመጣው የነሃሴ ወር የፍልሰተ ማርያም የጾም ወቅት ዝግጅት ምዕመናን ስለእውነተኛ ሰላም እንዲጸልዩ አጥብቀን እናሳስባለን።
3. ስለሰላም እንስራ
“ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” (ማቴ 5፡9) ይለናል ወንጌላዊው ማቴዎስ። ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሁላችንም ለሰላም እንድንሰራ ተጠርተናል። ይህም ለሰላም፣ ለእርቅ፣ ለፍትህ፣ ለሰው ልጅ ህይወት መከበር እና ፍጥረትን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ ቆራጥ መሆንን ይጠይቃል። በማህበረሰባችን ውስጥ ለሰላም የሚሰሩ ብዙ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። የሃይማኖት መሪዎች፣ ምዕመናን፣ ፖለቲከኞች፣ የማህበረሰብ አገልጋዮች፣ የእናቶችና የሴቶች የሰላም ቡድን፣ እንዲሁም ሰላምን የሚሹና ለሰላም የሚደክሙ ብዙ የወጣቶች መሪዎች አሉ። ለሰላም በምናደርገው ቁርጠኝነት ሁላችንም ሰላምን እንደምንፈልግ እንገነዘባለን። በአገራችን ያሉ የእግዚአብሔር ህዝቦች ለሰላም፣ ለእርቅ እና ለወንድማማችነት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጋር እንዲተባበሩ እንጋብዛለን። ይህ ቁርጠኝነት የሚወሰደው በእምነታችን ልምድ ጥሩ ነገርን ተስፋ በማድረግ እና በፍቅር፣ ወንድሞች እና እህቶች ውስጥ በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል የተፈጠርን የእያንዳንዳችን ክብር ያለን ሰው እየበዛን መሆናችንን በማወቅ ነው።
“ግጭቶች ሳይፈቱ፣ በተቃራኒው ተደብቀው ወይም ተቀብረው በዝምታ ሲቀሩ ወደ ከባድ ጥፋት እና ወደ ኃጢአት ተባባሪነት ያመራናል። ግጭት ሲያጋጥም ሁልጊዜ በውይይት እና በግልጽነት፣ በታማኝነት እና ትዕግስት በተሞላ መንፈስ በድርድር ሊፈታ ይገባዋል። በተለያዩ ቡድኖች መካከል ግጭት የጥላቻ ፍላጎት ከተወገደ ቀስ በቀስ በእውነተኛ ፍትህ ላይ መሰረት ወደሚያደርግ ውይይት ማደግ ይችላል። (ነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ፣ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” አንቀጽ 244)
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የሰላም ንግስት የሆነችው እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም ንግሥት የሁሉ አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር እንድታማልድን እና ሁላችንም የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ከፈጣሪ የተሰጠንን የሰላም ስጦታ ተቀብለን እንድንጠቀምበት፣ እንድንጠብቀው እና በመከራ ለሚሰቃዩት የእግዚአብሔር ሰዎች ማማለዷን እንድትቀጥል ደግመን እንማጸናታለን።
እግዚአብሔር ይባርከን፣ ይባካርችሁ!!!
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ሞጆ፤ ኢትዮጵያ።
