የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሃመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር ውይይት አድረጉ።
ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት አዲስ ከተሾሙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሃመድ እድሪስ ጋር ውይይት አድረጉ። መርሃግብሩ በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ መሪነት በመክፈቻ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን ብፁዕነታቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት፣ የተሳታፊዎችን ትውውቅ እና የውይይት ሀሳቦችን አጋርተዋል።
ብፁዓን ጳጳሳት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ተግዳሮቶች ከሆኑት ውስጥ የሚጠቀሱትን በተለይም ወቅታዊ የሀገራችን የሰላም ሁኔታ፣ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ህጋዊ ሰውነት እንዲሁም የውጪ ዜግነት ያላቸውን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የመኖሪያ ፍቃድ ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ በማስረዳት ከመንግስት የሚጠብቁትን ድጋፎች አጋርተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር በሰላም ዘርፍ በልዩ መልኩ እየሰራች ያለውን አጽንዖት ሰጥተው ከመንግስት ጋር በመተባበር በቀጣይ በተለይም በአሁን ወቅት የሀገሪቱን የሰላም ሁኔታ አንገብጋቢነት ባገናዘበ በጋራ የሚሰራባቸው አቅጣጫዎች ላይ ሀሳቦችን ሰጥተዋል። ይህ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ቢሆንም በቀጣይ ከቤተክርስቲያኒቷ ጋር በቅርበት በመመካከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ፣ አቶ መሃመድ እድሪስ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመቂ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ስዩም የሆሳዕና ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የእምድብር ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ክቡር አባ ከተማ አስፋው ጠቅላይ ጸኃፊ፣ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች እና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ክፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።