የ2013 የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በቅዱስ ፍራንቸስኮስ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተከበረ።
የ2013 የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በቅዱስ ፍራንቸስኮስ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተከበረ።
የ2013 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በዓል ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመሥዋዕተ ቅዳሴ፣ በዑደት እና በልዩ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ተከብሯል።
ክቡር አባ ገብርኤል ወልደሃና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ መሥዋዕተ ቅዳሴውን የመሩ ሲሆን ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሐዋርያዊ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ክቡር አባ ገብረወልድ ገብረጻድቅ በኢትዮጵያ የካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች የኪዳነምሕረት አውራጃ ዐለቃ፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን ተገኝተዋል።
ክቡር አባ ገብረወልድ ገብረ ጻድቅ የካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች የበላይ ዐለቃ በክብረ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት ቃለምዕዳን “የዘንድሮውን የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት በዓል የምናከብርበት ወቅት ከወረርሽኝ ስጋት ያልተላቀቅንበት የምንወዳት፣ የምናከብራትና መልካሙን ሁሉ የምንመኝላት ምድራችን ኢትዮጵያም በብዙ ችግሮች ተከብባ የምትገኝበት ወቅት ነው።
በጥምቀት ሁላችንም ያለአንዳች ልዩነት የእግዚአብሔር ልጆች እና የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደሶች ሆነናል። በመሆኑም እንደወንድማማች እና እህትማማቾች ሕይወታችንን በደስታ እና በነጻነት መምራት ይገባናል። መጠመቃችን ካለመጠመቅ የማይሻል ከሆነ ግን ለሰማይም ለመድርም እርባና ቤስ ነን። ክርስቲያኖች ተብለን መጠራታችን ክርስቶስን እንድንመስል የማይረዳን ከሆነ ዋጋችን ከንቱ ነው። በመሆኑም ሁላችንም ክርስቲያናዊ ጥሪያችንን የሚያስመሰግን ሕይወት እየኖርን መሆናችንን እንድንመረምር ተጋብዘናል። የየራሳችንን የጥምቀት መሃላዎች እንዴት እየኖርናቸው እንደሆነ ቆም ብለን ማስተዋል የሚገባን ጊዜ ላይ ነን።
ተልዕኳችን በዘመናችን ክርስቶስ በሕዝቦቹ መካከል ሕያው እና ድንቅ የሚያደርግብን ሕዋሳቶቹ መሆን ነው። ተልዕኳችን እንደ ክርስቶስ ሕግን የሚተላለፉትን፣ ፍትሕን የሚያጓድሉትን፣ ከእውነተኛው መንገድ ተንሸራትተው የሚቅበዘበዙትን በትህትና ወደ እውነት እንዲመለሱ መጋበዝ ነው። የተሰበሩትን መጠገን፣ ሰላም ላጡ የሰላም መልዕክተኞች መሆን፣ የፍቅር፣ የምሕረት ሥራዎች አምባሳደሮች መሆን ይጠበቅብናል። እጆቻችንም ምድራችንን ውብ እና ለሁሉም ምቹ መኖርያ እንድትሆን ለመሥራት ዝግጁ መሆን ያስፈልገናል” ብለዋል።