ርዕሰ አንቀጽ
የምሥራቹ ቃል ዛሬም ይሰማ
እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድህን ተወልወዶላችኋል፡፡ ይህም ብሩክ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሉቃ 2፡-12። ምሥራቹን የሚነግሩን ቅዱሳን መላዕክት ናቸው፡፡ ቅዱሳን መላዕክት በብርሃን እየኖሩ የእግዚአብሔርን ብርሃን አበሩ ፣ በቃላቸውም “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር በምድርም በጎ ፈቃድ ሆነ ( ሉቃ 2፡13) በማለት የምህረትን ዓመት አወጁልን።
የቅዱሳን መላዕክት ምስጋናና ዝማሬ፤ የእረኞች የተነገራቸው ቃል ሳይጠራጠሩ ማየታቸውና መደሰታቸው፣ የቅድስት ድንግል ማርያም በልቧ ውስጥ አምቃ የያዘችው ፀጋ፣ የምድር ፍጥረታት ደስታ የእግዚአብሔር ፍቅርና ምህረትን በጊዜና በቦታ እንደማይገደብ እኛም እንመሰክራለን፡፡
እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠ፡፡ ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም (ዮሐ 3፡-16)፡፡ ቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ በቃል መልክ የነበረው ሥጋ ለብሶ ከሰማያት ሰማያት ወርዶ ራሱን ዝቅ በማድረግ ወደ ሰዎች እንዲመጣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው መነሻና ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ለሰዎች ያለው ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ በሰው አእምሮ መረዳት የሚያዳግተውን መለኮታዊ ምሥጢር ለሰዎች ገለጠ፡፡ ይህም የዓለም ብርሃን፣ የሕይወት እንጀራ፣ መንገድና እውነት፤ ፍቅርና ሰላም የሆነው ልጁን ላከ፡፡
እግዚአብሔር የዓለም ፈጣሪ የሆነው ትልቁ ጌታ እንዴት የትንሹን ሰው መልክ መስሎ የሰው ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ በመገለጥ ማደሪያውን በሰዎች መካከል አደረገ የሚለው ምሥጢር ድንቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር በፍቅር ስለ ፍቅር ብዙዎችን ወደ ፍቅር መንገድ ለመምራት ብሎ አደረገው፡፡ እርሱ ዝቅ ያለው እርሱ የተዋረደው ብዙዎች ወደ ላይ ከፍ እንዲሉ፣ ብዙዎች እንዲከበሩ ነው፡፡ እርሱ ሕይወቱን የሰጠው ብዙዎች ዘላለማዊ ሕይወት እንዲያገኙ ነው፡፡ በእኛ መካከል ሥጋ ለብሶ ያደረው ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ለክርስቶስ ዛሬም እድናየውና እንድናውቀው ይጠራናል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል “ንጹሕ ልብ ያላቸው እግዚአብሔርን ስለሚያዩ ደስ ይበላቸው” (ማቴ 5 ፡-8) ይላል፡፡ የልብ ንጽሕና ማለት የእግዚአብሔርን ጸጋ የተላበሰ ሕይወት ማለት ነው፡፡ የልብ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለመኖር የሚጣጣሩ ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት መስርተው ይኖራሉ፡፡ በልባቸው ውስጥ በሚያድረው የእግዚአብሔር መንፈስ አማካይነት በውስጣዊ ልቦናቸው እግዚአብሔርን ያያሉ፡፡ እነርሱ በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን ያስቀድማሉ፤ በመንፈስ ከእርሱ ጋር ይወያያሉ የእርሱን ፈቃድ እየጠየቁ ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ከዓመተ ዓለም ወደ ዓመተ ምህረት ያስገባን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እኛም የዕድሉ ተጠቃሚ እንድንሆን ሁልጊዜ ያገኘነውን የበራልንን ብርሃን እንከተል አንልቀቅ፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2025 ዓ.ም. ላይ ደርሰናል፡፡ ዘመኑን በክርስቶስ ያገኘነውን ብርሃን ደግመን ደጋግመን እንድናሰላስለው ራሳችንን ወደ ውስጥ እንድንመለከት ቤተክርስቲያን እንደ ሁልጊዜው ጥሪ አድርጋልናለች፡፡ ምህረት ተቀባዮች ብቻ ሳይሆን ምህረት አድራጊዎች እንዲሁም ይቅር ባዮችና ይቅርታ አድራጊዎች መሆን መታደል ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የኢየቤልዩ ዘመን ስታውጅ ሰላምን በብቸኝነት የሚሰጠን ክርስቶስን በልባችንና ደግመን ደጋግመን በመኮትኮት መልካም ፍሬ አፍርተን ለተተኪያችን ማስተላለፍን አንርሳ፡፡
የክርስቶስን የልደት ቀን(ገና) ምክንያት አውቀውትም ሆነ ሳያውቁ በመላው ዓለም ይከበራል፡፡ ልዩነቱ ጊዜያዊውን ደስታ ተሻግሮ የማየት ጸጋ ካልተሰጠን እና ለማግኘት ጥረት ካላደረግን የክርስቶስ ልደት ትርጉሙን በቀላሉ መረዳት ቀላል አይደለም፡፡ ዘላለማዊ ደስታ የሚሰጠን አንድና አንድ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በዘመኑ ትንሽ የነበረችውና ዛሬ የዓለም መሰባሰቢያ እንደሆነችው ቤተልሔም መንደር ከፍ አድርገን የእግዚአብሔርን ምህርት እናውጅ፡፡
