በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የሊቀጳጳሳት እንደራሴ የሆኑትን ክቡር አባ ተስፋዬ ወልደማርያም በአሜሪካ እና ካናዳ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ
ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የሊቀጳጳሳት እንደራሴ የሆኑትን ክቡር አባ ተስፋዬ ወልደማርያምን ከሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአሜሪካ እና ካናዳ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ አድርገው የሾሙአቸው መሆኑን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጽዋል::
ክቡር አባ ተስፋዬ ወልደማርያም እ.አ.አ.በ1961 ዓ.ም. በአሊቴና ትግራይ ተወለዱ:: በእ.አ.አ. 1988 ዓ.ም. ማእረገ ክህነት ተቀበሉ:: በሮም የቅዱስ ቶማስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ በሞራል ቴዎሎጂ ከፍተኛ ትምህርት ተከታትለው አጠናቅቀዋል:; በአገልግሎት ዘመናቸውም በሀገር ውስጥ በተለያዪ የአገልግሎት ዘርፎች በተለይ በቅዱስ ፍራንቸስኮስ የፍልስፍና እና ነገረ መለኮት ተቅዋም ያገለገሉ ሲሆን ከሀገር ውጭ በሰሜን አሜሪካ በመቀመጥ ኢትዮጵያውያንን ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል:: በዋሽንግተን የሚኖሩ አፍሪካውያንን በማስተባበርም ይታወቃሉ:: በዋሽንግተን እጅግ ቅዱስ ምሥጢር ቁምስና ለሚከናወኑ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ረዳት አስተባባሪ በመሆን አገልግለዋል::
እ.አ.አ. 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የሊቀ ጳጳሳት እንደራሴ በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው::