በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚገኙ የወጣት ማህበራት እና እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች የስልጠና ምክክር እና የልምድ ልውውጥ ዝግጅት
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚገኙ የወጣት ማህበራት እና እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች የስልጠና ምክክር እና የልምድ ልውውጥ ዝግጅት በብሄራዊ ወጣቶች ቢሮ ከጥር 8 እሰከ 9 2013 ዓ.ም. በደብረዘይት የጋሊሊ የጽሞና ማዕከል ተዘጋጀ።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚገኙ አለምአቀፍ የወጣት ማህበራት እና እንቅስቃሴ አስተባባሪዎችን በብሄራዊ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገናኘ የስልጠና እና የምክክር መድረክ ተካሄደ።
ይህ ስልጠና ከሰባት ማህበራት እና ከሁለት ፕሮግራሞች የተሰባሰቡ ወጣት መሪዎችን ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለት ቀናት በቆየ የስልጠና መድረክ አገናኝቷል። የወጣት ቢሮው ይህንን ስልጠና ሲያዘጋጅ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የወጣት እንቅስቃሴዎች እና ማህበራት ለአንዲቷ ቤተክርስቲያን ግንባታ መዋል እንዲችሉ የሚለውን መሰረታዊ ዓላማ የያዘ ነበር። ይህንን ዓላማ ይበልጥ ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ ፅሁፎች ቀርበው ነበር። ከእነርሱም ውስጥ ስለ ቤተክርስቲያን መዋቅር ፣ ስለ ቤተክርስቲያን እና ልዩ የሆኑ የጸጋ ስጦታዎች(Church and Charism)፣ ስለ መለየት እና ሚዛናዊ አስተውሎት ጥቅም እና በማህበራት እና በእንቅስቃሴዎች በእስከዛሬ ጉዞ የግል ሕይወታችን ታንጸናል?፣ ቤተክርስቲያን ተጠቅማለች, ተገንብታለች? የሚለውን በመፈተሽ እና በመመርመር የተሻለ ለማድረግ አብሮ ለማቀድ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሐዋሪያዊ መልዕክቶች የሆኑት ክርስቶስ ሕያው ነው እና በቅርብ ጊዜ የወጣው ሁላችንም “ወንድማማቾች/እህትማማቾች ነን” የሚሉት ሐዋርያዊ መልዕክቶች ላይም ማጠቃለያ ተስጥቷል። አዲስ ስለተቋቋመው የወጣቶች ቢሮም መግለጫ ተደርጎ ሁሉም የወጣቶች እንቅስቃሴ እና ማህበራት በወጣት ቢሮው ስር በመሆን ከቢሮው ጋር እና እርስ በእርሳቸው በመረዳዳት እንዲሠሩ መድረክ ተፈጥሯል ። እነዚህን ዝግጅቶች ተከትሎ የፓናል ውይይት ጊዜ የነበረ ሲሆን በዚህም ወጣቶች ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸል።
አንዱ እንቅስቃሴ ከሌላው ጋር እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ለማድረግ የልምምድ ልውውጥ እና የእንቅስቃሴዎች አላማ እና መንፈሳዊነት ትውውቆቆችም ተደርገዋል። ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ዝግጅት ብዙ ስንቆችን ለእንቅስቃሴ እና ማህበራት አስተባባሪዎች ያስያዘ ሲሆን በቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸው ተግባራት ላይ በአብሮነት ከወጣት ቢሮው ጋር በትብብር ለመስራት እና በየሀገረስብከቱ የተጠናከረ ጥሩ የግንኙነት መረብ በመዘርጋት በአንድነት አንድ አካል በመሆን ለአንዲቷ ቤተክርስቲያን ለመስራት የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም የደብረዘይት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያንን በመጎብኘት ምዕመናንን በቤተክርስቲያን ያላቸውን ታላቅ አገልግሎት ለማየት እና ልምዳቸውን ለመካፈል ተችሏል። አስተያየታቸውን ከሰጡ ወጣቶች እንደተገለፀው በኘሮግራሙ መደሠታቸው እና ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃት እንዳገኙ ተናግረዋል።
ሁሉም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! የኢትዮጵያ ወጣቶች ቢሮ