በዓለም ዙርያ የሚገኙ ክርስቲያኖች 54ኛውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት እ. አ. አ. ከጃንዋሪ 18 – 25 ቀን 2021 ዓ.ም. በበይነ መረብ በጋራ ጸሎት አሳልፈዋል።
በዓለም ዙርያ የሚገኙ ክርስቲያኖች 54ኛውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት እ. አ. አ. ከጃንዋሪ 18 – 25 ቀን 2021 ዓ.ም. በበይነ መረብ በጋራ ጸሎት አሳልፈዋል። በሃገራችን ኢትዮጵያም የ2013 ዓ.ም. የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ከጥር 10 – 17 2013 ዓ.ም. እየተከበረ ያለ ሲሆን በዚህ የጸሎት ሳምንት ክርስቲያኖች በአብያተክርስቲያናት መካከል የመቀራረብ፥ የዕርቅ እና የአንድነት መንፈስ እንዲሰፍን ጸሎት እያደረጉ ቆይተዋል። ከመቶ ዓመታት በላይ ታሪክ ባለው በዚህ የጋራ የጸሎት ጉዞ ክርስቲያኖች “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” (ዮሐ 17፡21) ለሚለው የጌታ ጸሎት ተግባራዊ ምላሽ ይሰጣሉ።
በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት በጋራ ያዘጋጁት የዚህ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት የመዝጊያ ሥነሥርዓት የአብያተክርስቲያናት የበላይ ጠባቂ እረኞች፣ አባቶች መነኮሳት እና ምእመናን በተገኙበት እሑድ ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ 9:00 ጀምሮ በቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊክ ትምህርት ቤት በልዩ የአብያተክርስቲያናት የጋራ መንፈሳዊ መርሃግብር ተከብሯል። በመርሃግብሩ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ ክቡር መምህር አካለወልድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሰበካ፣ ክቡር ፓስተር ጻድቁ አብዶ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ሕብረት፣ ክቡር ወንድም ብርሃነ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነየሱስ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሲኖዶስ እንዲሁም ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ተገኝተው የጋራ ጸሎት እና የአብሮነት መልዕክት አስተላልፈዋል። በየበኩላቸው ባስተላልፉት መልዕክትም ያለንበት ወቅት ክርስቲያኖች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በመቀራረብ ሰለዓለማችን እና ሰለ ሀገራችን መጸለይ የሚገባን እንዲሁም በጋራ አብሮ በመሥራት የክርስቶስን ፍቅር መመስከር የሚገባን ጊዜ ነው ብለዋል።
በመርሃግብሩ ላይ ዓለማችንም ሆነች ሀገራችን በአሁኑ ወቅት የምትገኝበትን የጤና እና የጸጥታ ሁኔታዎች በተመለከተ አብያተክርስቲያናቱ የጋራ ጸሎት አድርገዋል፤ የክርስትና እምነት ተከታይ ምእመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ የሰላም መሳሪያ አንዲሆኑ፣ ከየእምነት ተቋማቶቻቸው ጋራ ለበጎ ሥራ እንዲሰለፉ ጥሪ አስተላልፈዋል።