ብፁዕ አቡነ ሮቤርቶ በርጋማስኪ አዲሱ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቀባበል ተደረገላቸው።
የባሮ ልጆች ዝማሬ ተሰማ ጋምቤላም ምስጋናዋን በዕልልታ አደረሰችክረምቱን የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ ሙላት ግንዱን እና ግማዱን ከወዲያ ወዲህ እያላተመ ሲጋልብ የነበረው የባሮ ወንዝ ጋብ ካለ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ዝናቡም ገታ ብሎ ሙቀቱ ወደ ቦታው ሊመለስ እያኮበኮበ ነው። ዐርብ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ የሆነ ልዩ ክስተት እንዳለ የከተማዋ ጎዳናዎች እና አደባባዮች ላይ የተሰቀሉት ባነሮች ይመሰክራሉ። “በየስፍራው አባታችን እንኳን ደህና መጡልን” የሚሉ መልዕክቶች በተለያዩ ቋንቋዎች ተለጥፈዋል። የብፁዕ አቡነ ሮብቤርቶ በርጋማስኪ አዲሱ የጋምቤላ ካቶሊካዊ ሰበካ ጳጳስ ምስልም አብሮ ተለጥፏል። የከተማዋ ሰማይ ይህችን ሁለት ቀናት ጣል ጣል ማድረግ ከጀመረው ዝናብ ሌላ መልካም ዜና ይዞ እየመጣላት መሆኑን ለመገንዘብ በጋምቤላ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተኮልኩሎ ሰማይ ሰማዩን በጉጉት የሚያየውን የጋምቤላ ነዋሪ መመልከት በቂ ነው። ልጅ አዋቂ፣ አዛውንት፣ ካህናት፣ ደናግል የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ ማንም አልቀረም። በገላጣው የአውሮፕላን ማረፊያ ተሰባስቧል። እንደተጠበቀው አልቀረም ከቀትር በኋላ ልክ በአስር ሰዓት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ET-151 አውሮፕላን የጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያን መሬት ረገጠች። በእርግጥ መልካም ዜናው ቀድሞ በስፍራው የደረሰ ቢሆንም ለአለፉት አምስት አመታት ገደማ ሁሉም በጉጉት ሲጠብቀው እና አምላኩን በጸሎት ሲማጸንበት የነበረው ለሰበካው አዲስ እረኛ የማግኘት ጉዳይ እውን የሚሆንበት ዕለት በመቃረቡ ደስታው፣ ዝማሬው፣ ሽብሸባው ልዩ ነበር። አበባ የያዙ ህጻናት ተደርድረዋል። በሰበካው አገልግሎት የሚሰጡ ካህናት፣ ደናግል በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ ቆመዋል። የጋምቤላ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ተንኩዋይ ጆን ጨምሮ የምክር ቤቱ የካቢኔ አባላት ከፊት ከተሰለፉት መካከል ይገኙበታል። ጥቂት ቆይቶ የኣውሮፕላኑ መውጫ በር ተከፈተ። ዕልልታው ቀለጠ። ዝማሬው ጸባዖት ለመድረስ ከልካይ አልነበረውም። አስቀድሞ በጋምቤላ ካቶሊካዊ ሰበካ የተመደቡትን አዲስ ጳጳስ አጅበው የተጓዙ የጅማ፣ የሆሳዓና፣ የባሕር ዳር – ደሴ ሀገረስብከቶች ጳጳሳት በየተራ ከአውሮፕላኑ ወረዱ። እያንዳንዳቸው ሞቅ ያለ ዕልልታ እና ዝማሬ ተቀበላቸው። በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ተወካይ የሆኑት ሞንሲኞር ዮሃንስ ጳውሎስም ከአጃቢ ጳጳሳቱ መካከል ይገኛሉ።በመጨረሻም በነጭ ልብሰ ጵጵስና የተካኑት ብፁዕ አቡነ ሮቤርቶ በርጋማስኪ አዲሱ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብቅ አሉ። በልዩ ትህትና እና ዝግ ባለ ሰላምታ ሕዝቡን ከርቀት እየባረኩ ከአውሮፕላኑ ወረዱ። የጋምቤላ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዕልልታ ቀለጠች። የምስጋና ዝማሬዎች ከዳር እዳር ተሰሙ። መዘምራን የሚያቆማቸው አልተገኘም። ካህናት ደናግል በደስታ አሸበሸቡ። “የእንኳን ደህና መጡልን” መዝሙሮች በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘመሩ። ህጻናት ቀርበው እንግዶቻቸውን ሁሉ በአበባ ሰጦታ ተቀበሉ። በመጨረሻም የሰበከው የእስከዛሬ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ክቡር አባ ተስፋዬ ጴጥሮስ የክልሉን ምክትል ፕሬዝዳንት እና ከፍተኛ የካቢኔ አባላት ወደ እንግዶቹ ፊት ይዘው በመቅረብ አንድ በአንድ አስተዋወቁ። ካህናት፣ ደናግል፣ መዘምራን እና ምእመናን በሙሉ ለአዲሱ ጳጳሳቸው ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ጉዞ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ የጋምቤላ ካቶሊካዊ ሰበካ ካቴድራል ተጀመረ። የአውሮፕላን ማረፊያው የአቀባበል ሥነሥርዓት እንዳበቃ በልዩ ዝማሬ፣ የመኪና እና የሞተር ሳይክል ጥሩንባ አጀብ በጋምቤላ ጎዳናዎች እና አደባባዮች ላይ ጋራ ቀኝ የተኮለኮለው ሕዝብ ለትንግርት እየተመለከተ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊክ ካቴድራል ደረስን። በቤተክርስቲያኑ አጠር ያለች የአቀባበል ሥነሥርዓት ከተከናወነ በኋላ እንግዶች ወደየማረፊያቸው ምእመናንም ወደ የቤታቸው ገቡ። እንዲህ ሆና ያች ቀን አለፈች። ደግሞ ለማግስቱ ለዕለተ ቅዳሜ የጵጵስና መንበር ርክክብ ቀጠሮ ተያዘ።