የአዲግራት ሀረገስብከት ጳጳስ ለነፍስኄር አባ ዲትማር ለንፈርስ የስንብት መልዕክት አስተላለፉ።

ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ መድህን ለነፍስኄር አባ ዲትማር ለንፈርስ ስንብት የሀዘን መግለጫ እና የአብሮነት መልዕክት አስተላልፈዋል። ሀምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከዚህ አለም ድካም ያረፉት ክቡር አባ ዲትማር የአፍሪካ ሚስዮናውያን ገዳም አባል ሲሆኑ በኢትዮጵያ ከሶስት አስርት አመታት በላይ በተለይም በፍልስፍና አስተምህሮ፣ የነገረመለኮት እና የሥርዓተ ሉጡርጊያ ጽሁፎችን በማዘጋጀት እና ለህትመት በማቅረብ የላቀ አስተዋጽዖ አድርገዋል።
ብፁዕ አባታችን በመግለጫቸው የክቡር አባ ዲትማርን በርካታ እና ዘርፈ ብዙ በጎ ምግባራትን የገለጹ ሲሆን በተለይም ከአዲግራት ሀገረስብከት እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ የፍልስፍና፣ የነገረመለኮት፣ የሥርዓተ ሉጡርጊያ፣ እና ሌሎችም ጽሁፎችን በትግርኛ እና በግዕዝ ቋንቋ እንዲዘጋጅ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም የሀገረስብከቱን ጳጳሳት በኩሪያ አወቃወር፣ የሐዋርያዊ እና የልማት ጽ/ቤት አደረጃጀት እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፍ አስተዋጽዖ አድርገዋል።
ክቡር አባ ዲትማር በቴክኖሎጂ ዘርፍ በኮምፒውተር ሥልጠና፣ ታዳሽ ኃይል አጠቃቀም እና የሀገረስብከቱን ካቴድራል የድምጽ ማጉያ ቁሳቁሶችን በመዘርጋት ያለድካም በትጋት ማገልገላቸውን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በዕድሜ የገፉ ካህናት ድጋፍ ለማደረግ በሚደረገው ጥረትም ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ብጹዕነታቸው ገልጸዋል።
የክቡር አባ ዲትማር በጽናት፣ በተግባር፣ በመንፈሳዊነት፣ በሰብዓዊነት እና በጽኑ ታማኝነት የተሞላ አገልግሎት እና ሚሲዮናዊ ህይወት የአዲግራት ሀገረስብከት እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሁሌም እንደሚያስታውሳቸው ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ለክቡር አባ ዲትማር ወዳጅ ቤተሰቦች፣ ለአፍሪካ ሚሲዮናውያን ገዳም በአለም አቀፍ እና በኢትዮጵያ ለሚገኙ አባላት መጽናናትን ተመኝተው በጸሎት ህብረት አብሮነታቸውን ገልጽዋል።
