የአዲግራት ሀገረስብከትን የጎብኙት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ልዑካን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
የአዲግራት ሀገረስብከትን የጎብኙት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ልዑካን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በአዲግራት ሀገረስብከት ከጥር 4 እስከ 6 2013 ዓ.ም. ጉብኝት አድርገው የተመለሱት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ልዑካን እንደገለጹት በመላው ትግራይ የሚገኙትን የጦርነት ተጎጂዎች በአፋጣኝ ለመድረስ እንዲቻል ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ክቡር ዶ/ር ሙሉ ነጋ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ክቡር አቶ አብርሃ ደስታ ጊዜያዊ ምክትል አስተዳደር እና ክቡር አቶ አበበ ገብረሕይወት የተገኙ ሲሆን በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በኩል ክቡር ዶ/ር አባ ተሾመ ፍቅሬ ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ የማሕበራዊ ልማት ዳይሬክተር፣ የካቶሊክ እርዳታ ድርጅተከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከአዲግራት ሀገረስብከት ክቡር አባ አብርሃ ሐጎስ የአዲግራት ካቶሊካዊ ሰበካ ዳይሬክተር፣ ክቡር አባ ወልደማርያም የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና ሲስተር መድኅን ተስፋዬ የፍቅር ሥራ እህቶች የፕሮጀክት አስተባባሪ ተገኝተዋል።
በተከታታይ ባደረጓቸው ሁለት ስብሰባዎችም በቀጣይ በመላው ትግራይ የሚገኙ ተጎጂዎችን በአፋጣኝ መድረስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ በዝርዝር በመወያየት ለዚሁ ዓላማ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የጋራ ግብረሃይል አቋቁመዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ የክልሉን ሰላም እና መረጋጋት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን መሰረተ ልማቶችን በመጠገን በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለማስገባት በሙሉ ኃይሉ እየሠራ መሆኑን አሳውቋል።
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተወካዮችም ለምግብ እና ለመድኃኒት ድጋፍ የሚሆኑ ግብይቶችን ለመፈጸም እና ከቦታ ቦታ በአፋጣኝ ለማጓጓዝ እንዲቻል የባንክ አገልግሎት ማነቆ እንዳይሆን እና የገንዘብ ዝውውርም ለጊዜውም ቢሆን በልዩ ሁኔታ መስተናገድ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲያመቻች አሳስበዋል።