የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በአዲግራት ሀገረስብከት ጉብኝት አድርጎ ተመለሰ
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በአዲግራት ሀገረስብከት ጉብኝት አድርጎ ተመለሰ
ክቡር ዶ/ር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ እና እና ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን ዳይሬክተር በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ጥያቄ ከጥር4 እስከ 6 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤን በመወከል በአዲግራት ካቶሊካዊ ሰበካ ጉብኝት አድርገው መመለሳቸውን ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የልዑካን ቡድን አባላቱ በጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ባደረጉት ገለጻ አስረድተዋል።
በመርሃግብሩ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሥራ አመራር ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የገዳማት የበላይ ዐለቆች ጉባኤ፣ ካህናት፣ ደናግል፣ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት የልማት ድርጅቶች ጥምረት (Act Alliance) ተገኝተዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ለተሳታፊዎች ሰለጉብኝታቸው ባቀረቡት ሪፖርት የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ መድህን ጋር በአካል የተገናኙ፣ እንዲሁም በሰበካው የሚገኙ መነኮሳት እና ካህናትን የጎበኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማም አብሮነታችንን ለማሳየት፣ በሰበካው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመቃኘት እንዲሁም ከብፁዕነታቸው የሰበካው ጳጳስ የሚቀርበውን መግለጫ ለማዳመጥም ጭምር ነበር፡፡ ክቡር አባ ተሾመ እንደገለጹት ይህንን ጉብኝት ማደረጋቸው እጅግ አስፈላጊ እና በአካባቢው የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ለመረዳት የሚረዳ ሆኖ አግኝተውታል።
ክቡር አባ ተሾመ በዚሁ አጋጣሚ ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ በመንበራቸው ላይ በመልካም ደህንነት የሚገኙ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ካሉ በኋላ ሁላችሁም ዘወትር በጸሎት እንደምታስቧቸው ይገነዘባሉ። በእኛ በኩል ላደረሳችኋቸው መልካም ምኞቶች እና ዘወትር በጸሎታችሁ የምታስቧቸው ስለመሆኑም ምስጋናቸውን አድርሰዋችኋል ብለዋል።
በመርሃግብሩ ላይ ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ ባቀረቡት ገለጻ በግጭቱ ምክንያት በክልሉ የደረሰውን ጉዳት ከሞላ ጎደል ለተሳታፊዎች አስቃኝተዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ሕንጻ ቤተክርስቲያኖች፣ የመድሃኒት መደብሮች፣ የህክምና ማዕከላት ሌሎች የመንግሥት፣ የግል፣ የሕዝብ እና የቤተክርስቲያን አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለጉዳት እና ለዘረፋ የተጋለጡ መሆናቸውን መመልከት ተችሏል። እንዲሁም በክልሉ በርካታ ሕዝቦች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ፣ ከሦስት ወራት ላላነሱ ጊዜያት ያለደሞዝ፣ ያለ ንግድ እንቅስቃሴ የቆዩ በመሆኑ የዕለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊው ቁጥር እጅግ ጨምሯል።
በመርሃግብሩ ላይ ከልዑካን ቡድኑ በተጨማሪ ወደ እዳጋ ሐሙስ ተጉዘው የተመለሱ አንዲት መነኩሴ እና በአድዋ፣ እና ሽረ ከሚገኙ ገዳማት አባላቶቻቸው መረጃ የደረሳቸው ሌሎች መነኮሳት በግጭቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በተካሄደው ውይይት ላይ በመገኘት በአሁኑ ወቅት ለተቸገሩ እና አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በአፋጣኝ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። የልዑካን ቡድኑ ስፍራው ድረስ በመጓዝ ላበረከተው አስተዋጽዖ፣ ለፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ትብብር ለሚያደርጉ በሙሉ እና እስካሁን ለተከናወኑት ሥራዎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተጨማሪም ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን ዳይሬክተር እንዳስረዱት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ግጭቱ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ከሌሎች የእምነት ተቋማት፣ ከኖርዌይ ቤተክርስቲያን እርዳታ ድርጅት፣ ከዓለም የአብያተክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት የልማት ድርጅቶች ጥምረት ከሆነው አክት አሊያንስ ጋር ድጋፍ ማድረስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በትብብር ስትሠራ ቆይታለች።
በአዲግራት ሀገረስብከት ከቤተክርስቲያን እና ከክልሉ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በተደረገው ውይይት መሰረት የተውጣጣ ግብረ ሃይል የተቋቋመ መሆኑ በልዑካን ቡድኑ በተገለጸው መሰረት ድጋፍ ለማድረስ ተግዳሮት የሚሆኑ የመጓጓዣ፣ የገንዘብ ዝውውር እና ወደ ተጎጂው ማሕበረሰብ ለመድረስ የሚያስችል ሕዝባዊ አስተዳደር መዋቅርን የተመለከቱ አንኳር ጉዳዮች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት፣ የቤተክርስቲያን እና የሕዝብ ማሕበራት ጋር በመወያየት በአፋጣኝ ወደ ተግባር መግባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በስፍራው አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረስ ያስፈልጋል ብላ ካቀደችው እርዳታ በአሁኑ ወቅት 31 በመቶ የሚሆነውን ማሰባሰብ የቻለች መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ 16,695,090.00 ብር የሚገመቱ በጥሬ ብር እና በዓይነት ድጋፍ ማሰባሰብዋን አብራርተዋል። ሆኖም ገና ብዙ የሚቀር በመሆኑ ድጋፍ አድራጊ አጋር አካላት በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዓለም ካሪታስ (Caritas Internationalis) ጋር ተጨማሪ ትብብር ማድረግ ሰለሚቻልባቸው ሁኔታዎች የቪዲዮ ውይይት ለማድረግ እቅድ የተያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” (ማቴ. 5 ፥9) በሚል በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ወደ ግጭት የሚያመሩ ሆኔታዎች በአፋጣኝ እንዲቆሙ እና ሁሉም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይኸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው እና በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን በመግለጽ በተከታታይ ለሁለት ጊዜያት የሰላም ጥሪ በይፋ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።