የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈትቤት ሠራተኞች የምስጋና ቀን
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ሠራተኞች የምስጋና ቀንን በመሥዋዕተ ቅዳሴ አከበሩ
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ሠራተኞች የ2012 ዓ.ም. የምስጋና ቀንን ሐሙስ ጳጉሜ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በልደተ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል በመሥዋዕተ ቅዳሴ አክብረው ውለዋል።
መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ (ዶ/ር) በመላው ሀገሪቱ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት ውስጥ አገልግሎት አያበረከቱ ያሉ ሠራተኞችን በሙሉ በየሙያ ዘርፉ እየጠሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ክቡርነታቸው “በተለይ በዚህ መላይቱ ዓለም በተፈተነችበት የወረርሽኝ ወቅት ከቤታችሁ ሆናችሁ በመሥራትም ይሁን በቢሮ በመገኘት ቤተክርስቲያን የጣለችባችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ላሳያችሁት ቀና ትብብር ለሁላችሁም ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል” ብለዋል።
“በተለይ በካቶሊክ የጤና ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ የምትገኙ የጤና ባለሞያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በሙሉ ምስጋናችን ካላችሁበት ይድረሳችሁ በማለት ዘወትር በጸሎት ከእናንተ ጋር መሆናችንን ላረጋግጥላችሁ እወድዳለሁ” ብለዋል።
የልደታማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ቆሞስ ክቡር አባ ታምራት ጡምደዶ በበኩላቸው ለጽ/ቤቱ ሠራተኞች “በገዛ ቁምስናችሁ ተገኝታችሁ በምስጋና አብራችሁን ማሳለፋቸሁ ለቁምስናችን ከፍተኛ በረከትን የሚያስገኝ መሆኑን ለመግለጽ እወድዳለሁ” ብለዋል። አያይዘውም ዘመኑ የመልካም አገልግሎት እና የወንጌል ምስክርነት ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።
ከመሥዋዕተ ቅዳሴው በኋላ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በተካሄደው የምስጋና ክብረ በዓል ላይ በወጣቶች ቢሮ አስተባባሪነት ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የተዘጋጀው “ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው መጽሐፍ በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ተባርኮ ለአገልግሎት ተሰራጭቷል።
“ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው ሰነድ እ.አ.አ. በ2018 ከተከናወነው የወጣቶች ሲኖዶስ በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተለይ ለወጣቶች የተላለፈ ሐዋርያዊ መልዕክት ነው።
ይኸው በላቲን ቋንቋ “CHRISTUS VIVIT” በሚል ለወጣቶች የተላለፈው ሐዋርያዊ መልዕክት ወደ አማርኛ የተመለሰው የካፑቺን ገዳም አባት በሆኑት በክቡር አባ ዳንኤል አሰፋ መሆኑ ተገልጿል።
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደርም ለመላው የጽ/ቤቱ ሠራተኞች መልካም መኞቱን በመግለጽ ከማክሰኞ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መደበኛው የሙሉ ቀን የሥራ ሂደት የሚጀመር በመሆኑ ሠራተኞች አስፈላጊውን የመከላከያ ጥንቃቄ እያደረጉ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ አሳስቧል።