የቅዱስ አቡነ ብሩክ ካቶሊክ መጽሃፍት መደብር ተከፈተ።
የቅዱስ አቡነ ብሩክ ካቶሊክ መጽሃፍት መደብር ተከፈተ

የቅድስት ስላሴ ቅዱስ አቡነ ብሩክ የመነኮሳት ገዳም መስራች እና የገዳሙ አስተዳዳሪ የሆኑት እማሆይ ሃረገወይን ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሐዋሪያዊ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ከሆነው የመጸሀፈ ነዋያት ቅዱሳት መሸጫ እና ሀይማኖታዊ መጸሀፍት ማከፋፈያ መደብር በሰፊው አገልግሎቶችን ለመስጠት የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ከሆኑት ክቡር አባ ከተማ አስፋው ጋር ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረጉት ስምምነት መሰረት መጸሀፍት መደብሩን ተረክበው በይፋ ከፍተዋል ።
መደብሩ ከዚህ በፊት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች በተጨማሪ እራሳቸው የሚሰሯቸው እና ከሌላ ሃገራት የሚያስመጧቸው የተለያዩ የቅዳሴ አልባሳት ( የካህናት እና የዲያቆናት፣ የመንበር ታቦት፣ እንዲሁም የጽዋ ልብሶች)፣ ህብስት፣ የቅዱሳን ምስሎች እና ሀውልቶች፣ ለቤተክርስቲያን የሚሆኑ ጥሩ መአዛ ያላቸው እጣኖች፣ ሻማዎች፣ መቁጠሪያዎች፣ ቀለበቶች፣ ለህጻናት፣ ለወጣቶች፣ ለደናግል፣ ለካህናት፣ ለምዕመናን የሚሆኑ የተለያዩ መንፈሳዊ መጽሐፎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉመው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
በተለያዩ በዓላት እና ፕሮግራሞች በሚኖርበት ጊዜም በቦታው በመገኘት መንፈሳዊ እቃዎች እንደሚያቀርቡ፤ በኢትዮጵያ ለተለያዩ ሀገረ ስብከቶችም ሆነ ምዕመናን የፈልጓቸውን እቃዎች በትዕዛዝ ሰርተው እንደሚልኩ ገልጸው ግለሰቦችም ሆኑ ማህበራት ማቅረብ የሚፈልጓቸው መንፈሳዊ እቃዎች ካሏቸው ለመደብሩ እንዲያቀርቡ ጋብዘዋል ።
እንዲሁም አሁን ባለው ሁኔታ የስራ ሰአታቸው ከዘወትር ሰኞ እስከ ዓርብ ባለው ጊዜ ከጠዋቱ 2:00-11:00 ሲሆን ዘወትር ቅዳሜ ደግሞ 2:00 – 6:30 እንደሚሆን አሳውቀው ለወደፊት የሰዓት ማሻሻያ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ገዳማውያቱ “እማሆይ” የሚል ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን ይህ ማዕረግ “ሁሉም ሴቶች እናቶች ናቸው” የሚለውን እምነት የሚያንፀባርቅ እና ከገዳሙ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ወላጅ እናቶች እንደሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ገዳናውያት እህቶች በመሆን ለሁሉም ሰው መንፈሳዊ እናት ለመሆን ሕይወታቸውን የሰጡ መሆናቸውን ለመግለጽ ነው። ገዳሙ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ 40ኪ.ሜ. ርቀት በሚገኘው ሆለታ ቤተክርስቲያን እና የገዳማውያቱ ማረፍያ የገነባ ሲሆን፤ በተጨማሪም የሕፃናት መዋያ በመገንባት በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ሕፃናት የትምህርት ዕድል አመቻችቷል።
ገዳሙም እራሱን ችሎ ለመቆም የተለያዩ ሥዎቸን እየሰራ የገኛል ከነዛም መካከል የግብርና ስራ፣ ዶሮ እና እንቁላል እንዲሁም የከብት እርባታ የመሳሰሉ የግብርና ሥራዎችን በመስራት ላይ የገኛሉ ። ከዚህም በተጨማሪ ለአካባቢው ሴቶች እና እናቶች የማማከር እና የተለያዩ ስልጠናዎችን በማመቻቸት የሚያግዝ ገዳም ሆኗል።






