59ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ።

ከህዳር 29 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በእምድብር ሀገረስብከት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሲካሄድ የቆየው 59ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ተጠናቀቀ።
ጉባኤው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መሰረታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ በመወያየት እጅግ ፍሬአማ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለይም የአዳዲስ ብፁዓን ጳጳሳት በጉባኤው መኖር የተሻለ አቅም የፈጠረና በጉባኤው የጎደሉ የኃላፊነት ቦታዎችን ተወካይ ጳጳሳት መሾማቸው ተገልጿል። ጉባኤው መዋቅራዊ ለውጦችን ያደረገ ሲሆን ከነዚህም መካከል የጉባኤው ፕሬዝደንት የሆኑትን ከብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ጋር በጋራ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ በምክትል ፕሬዝደንትነት እና ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የእምድብር ሀገረስብከት ጳጳስ የጉባኤው ቋሚ ጽኃፊ በመሆን እንዲያገለግሉ በተጨማሪም የጉባኤው ቋሚ ኮሚሽን ተጠናክሮ እንዲመሰረት ጉባኤው ወስኗል። ጉባኤው በብፁዓን ጳጳሳት የሚመሩትን ከ10 በላይ ኮሚሽኖችም ላይ በመወያየት መሪ ጳጳሳትን የመደበ ሲሆን የሥያሜ እና ሌሎች ማሻሻያዎችን ማድረጉ ተገልጿል። እ.ኤ.አ በ2014 የተዘጋጀው የጉባኤው መተዳደሪያ ደንብ ላይ አስፈላጊ ማሻሻያዎች በማድረግ ለቅድስት መንበር እንዲላክ ወስኗል።
የጉባኤው ማህበራዊ ተግባቦት ኮሚሽን ተወካይ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ የባህርዳር ደሴ ሀገረስብከት ጳጳስ እንደገለጹት ጉባኤው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተካሄደ እና ታሪካዊ የአብሮነት ውሳኔዎች የተደረገበት ልዩ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የሁሉም ሀገርስብከቶችን ነባራዊ ሁኔታዎች በጥልቀት እና በመደማመጥ መወያየታቸውን የገለጹ ሲሆን በተለይም በአዲግራት ሀገረስብከት ባለው ሁኔታ በአብሮነት እና በመደጋገፍ መጓዝ የሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል።
የቤተክርስቲያን ተቋማት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነው የቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን በተጨማሪም ሌላኛው የጉባኤው ተቋም የሆነው የወሊሶ ቅዱስ ሉቃስ ካቶሊክ ሆስፒታል 25ኛ የምስረታ ዓመትን ማክበራቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው የጉባኤው ዋና አጀንዳ የነበረው የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ ሲሆን ለሀገር እድገት መሰረታዊ ነገር ሰላም መስፈን መሆኑን ገልጸዋል። “እንደሀገር ያለውን እድገት የሚበረታታ ቢሆንም ለሀገርም ሆነ ለዜጎች ዘላቂ እድገት ሰላም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልዩ መገለጫዎቿ የሆኑት የምስራቅ እና የምዕራብ ሥርዓቶቿ ሥርዓተ ሉጡርጊያ ላይ በዚህ ጉባኤ በጥልቀት በመወያየት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ህብረቷን ያጠነከረችበት መሆኑ ተገልጿል። በሲኖዶስ አብሮ በመጓዝ ሂደትም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሰበካዎች በአንድነት እና በተስፋ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። የሲኖዶሱ የመጨረሻውን ሰነድም እንደየሰበካው ተጨባጭ ሁኔታ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ካታኪስቶች እና መላው ምዕመናን በህብረት አብረው እንዲጓዙ ጥሪ ቀርቧል።
