ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትየጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ2013 ዓ.ም የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል መልዕክት
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትየጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት
የ2013 ዓ.ም የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓልን አስመልከተው ለመላው ምዕመናን
ያስተላለፉት መልዕክት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
‹‹አንተ ግን ያው አንተ ነህ፣ የዕድሜህም ዘመን ወሰን የለውም፣ ዓመቶችህም
ከቶ አያልቁም›› (መዝ.102፡ 27)
ብፁዐን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያንና /ገዳማውያት
ክቡራን ምዕመናን
በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ
ክቡራትና ክቡራን
ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ምዕመናን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ
ዘመነ ማቴዎስ የ2013 ዓ.ም የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል በሰላም
አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን አቀርባለቸኋለሁ፡፡
እግዚአብሔር አባታችን በእርሱ ዘንድ ከማያልቀው ዓመታቱ ውስጥ እነሆ
አሁን ደግሞ አዲስ ዓመትን ስጥቶናል፡፡ እኛም ሁላችን እግዚአብሔር ስለ ሰጠን
ዓመት እናመሰግነዋለን፡፡ እግዚአብሔር አዲስ ዓመት የሚሰጠን ለሰዎች ደስ
ለሚያሰኝ ጥቅምና እርሱ ለሚፈልገው ነገር መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር ለኛ በምድር ላይ ለምንኖረው በፍቅሩ ብዙ ነገር ያደረገልን ሲሆን
በማያልቀው ጸጋው ዝናብን፣ ወንዞችን፣ ኮረብታዎችን፣ ሜዳዎችን አቦቦችን
የሚያለመልም የፀሐይ ብርሃንን ይስጠናል፡፡ እኛ ሕያዋንንም እንደ በጎ ፈቃዱ
ያኖረናልም የሁላችንንም ፍላጎት ያረካል፡፡ አዲስ ዓመት ለእኛ ከእግዚአብሔር
የሚስጠን ነው፡፡ ይህም በያዕቆብ መልእክት 1፡17 ላይ እንደሚገኘዉ
‹‹መልካም ስጦታና ፍፁም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው›› ይለናል
ስለሆነም ይህን ስጦታ ተቀብለን በፈጣሪያችን ተስፋ አድርገን ዓመቱን
እንጀምረዋለን፡፡
በአሳለፍነው ዓመት ብዙ ነገሮቻችንን ልናሳካ አስበንና አቅደን ዓመቱን
ጀምረነው ነበር፡፡ ሆኖም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አማካኝነት እንዲሁም በተለያዩ
ነገሮች ከባድና መራራ ጊዜያትን ያሳለፍንበት ነበር፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት
ገበታቸው፣ ሠራተኞች ከሥራ ቦታቸው በቤት እንዲቆዩ የሆነበትና በእምነት
ቦታዎቻችን ላይ እንደ ልብ እንዳንጸልይና እንዳንሰባሰብ ያገደን፣ ሰውና ሰውን
ያራራቀ ብዙ ዜጎቻችንን ያሳመመብንና የሰው ሕይወት የጠፋበት፣ የእርስ በእርስ
ግጭት የበረታበት፣ ሕይወት በሳዛኝ ሁኔታ ያለፈበት፣ ንብረቶች የወደሙበት፤
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የጎርፍ አደጋ ያጋጠሙበት በአጠቃላይ የሕይወት
ደስታን ያጣንበት ከፊል ብርሃን ከፊል ጽልመት ሆኖ አልፎአል፡፡
በትን. ኢሳ 45፡18 ‹‹እግዚአብሔር ሰማያትን ፈጠረ፣ አምላክ እርሱ
ብቻ ነው፡፡ ምድርን በቅርጽ አሳምሮ ሠራ፣ ለዘለዓለም እንዳትናወጥ አደረጋት፣
ለሕዝቦች መኖሪያ እንድትሆን እንጂ እንድትጠፋ አይደለም›› ይለናል፡፡
እግዚአብሔር ከፈጠረው ምድር ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ እርሷም
ለሁላችንም መኖሪያና መገለጫ ጥላችን ሆና ኖራለችም ወደፊትም ትኖራለች፡፡
እርሱ በሰጠን የተፈጥሮ ምድር ሁላችንም በነፃ አየኖርን በጋራ ክረምቱን፣
በጋውን እኩል ተቀብለን እየኖርን አሁን ላይ ሕይወትን በሚያናውጡ ችግሮች
ተከብበን እንገኛለን፡፡ የእርሱ ፍጥረት የሆኑ አእዋፋት እንኳን ያለ ምንም
ከልካይ ከቦታ ቦታ በነፃነት እየተንቀሳቀሱ በፈለጉበት ቦታ ላይ ይበርራሉ
ጎጇቸውንም ይሠራሉ፡ የእግዚአብሔር ሥራ ግሩም ነውና፡፡
በተቃራኒው እግዚአብሔር በአርዓያና በአምሳሉ የፈጠረን ሰዎች ይህችን
አገራችንን በተለያዩ መንገዶች ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅርን፣ የአንድነት
ተምሳሌትነቱን እያጠፋን ሕዝቦቻችን በሐዘንና በስጋት በለቅሶና በፍርሃት
የሚኖሩባት እንድትሆን እያደረግናት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የእምነት መጨለምና
የተስፋ ማነስ፣ የነገሮች ማዕበሎች ወደሚፈልጉበት ወደብ የሚወስዱን እኔነት
የሚል አካሄድ ስለበዛ ነው፡፡ ከዚህ ሁኔታ ለመዳን ወደ ፈጣሪ ልባችንን
መመለስ ያስፈልጋል፡፡
አዲሱን ዓመት በተስፋ ተሞልተን ልንቀበለው ያስፍልጋል፡፡ ይህም በፀሎት
ሊሆን ይገባል፡፡ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያላቸው እምነት ፍፁም እንደሆነ፣
እኛም በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ፍፁም እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ፈጣሪ
ሕይወትን የሰጠን ለሌሎች ጥቅም እንድናውለው እንጂ ለራሳችን ብቻ ልንይዘው
አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ለሰው ማሰብና መኖር ይኖርበታል፡፡ በትክክልና
በእውነት ተዛምዶ በጋራ ዓላማ መመሪያና የጋራ ፍላጎት ያለው ዓላማ ኑሮአችንን
ከጭንቀትና ከሃሳብ አውጥተን በሰላም የምንኖርበትና የምንንቀሳቀስበት
የደስታ ዓመትና ጊዜ እግዚአብሔር እንዲሰጠን ልንለምን ያስፈልጋል፡፡ ይህንን
ከባድ ጊዜ በእግዚአብሔር ቃል በመታመንና በመመርኮዝ ማለፍ አስፈላጊ
ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹በሀዘናችሁ አያችኋለሁ፣ ነገር ግን እንደገናም
አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል›› (ዮሐ 16፡20) ይላል፡፡ ምንም ብናዝን
ቃሉ ያፅናናል፣ ያበረታናል፡፡ ፈጣሪያችንን የምንወድ ሁሉ ድርጊቶቻችን ክፉውን
ነገር ጥሉ የሚለውን ቃል የሚያስረሳን መሆን የለበትም፡፡ ለትልቁ አምላክ
መገዛት ወደ መልካም ሃሳብ ይመራናል፡፡
መንግሥት በየትኛውም በኩል የዜጎች ከለላና መብት ከመሆኑም በላይ
የዜጎቹን ደህንነት፣ ሰላምና የመኖር ዋስትና በሚገባ ሊያረጋግጥና ሊያሰፍን
ይገባል፡፡ አሁን ያለውም ትውልድ በአንድነትና በሕብረት በመቆም ለመጪው
ትውልድ መልካም ነገር መሥራትና ማቆየት ያስፈልገዋል፡፡
የተወደዳችሁ ምዕመናን
በዚህ የበዓል ጊዜ ልግስናችሁን አብዝታችሁ እንድታደርጉ አደራ ማለት
እወድዳለሁ፡፡ ምክንያቱም በኮሮና ወረርሽኝና በተለያዩ ችግሮች በቤት ውስጥና
በውጪ በችግር ላይ ለሚገኙት ሁሉ፣ በምንችለው አቅም ሁሉ፣ ሰዎችን
እንድናግዛቸውና እንድንረዳችው አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆንልን፤
የእምነት፣ የዘርና የጎሣ ተቃርኖ የሚጠፋበት ሰውና ሰው የሚዋደድበትና
የሚተሳሰብበት፤ የምሕረቱና የይቅርታው መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሞላ ተስፋ
የምናደርግበት እንዲሆንና የኮቪድ ወረርሽኝ ከአገራችንና ከመላው ዓለም
እንዲወገድልን ተግትን እንጸልይ፡፡ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅና በምዕራብ
የሚገኙትን ህዝቦቻችንና አገራችንን ይባርክልንና ይጠብቅልን፡፡
በመጨረሻም በውጪ የምትኖሩና የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ
ኢትዮጵያውያን፤ በየሕክምናው ጣቢያ በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰባችሁ ተለይታችሁ
የሕክምና አግልግሎት በመስጠት ላይ ያላችሁ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ የጤና
ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፤ የህብረተሰብ ጤና ሠራተኞች፣ የተለያዩ አገልግሎት
የምትሰጡ የአንቡላንስ አሽከርካሪዎች፣ የእሳት አደጋ ባለሞያዎችና ሌሎችም
በተለይ የአገር ድንበርን ለማስከበር በየድንበሩና በተለያዩ ቦታዎች ግዴታችሁን
የምትፈፅሙ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት በሙሉ፣ በየቤቱና
በየሐኪም ቤቱ በህመም ላይ የምትገኙ እግዚአብሔር በምሕረቱ
እንዲምራችሁ፤ በማረሚያ ቤቶች የምትገኙትን እግዚአብሔር እንዲፈታችሁ፤
በስደት ላይ ያላችሁትን እግዚአብሔር ለአገራችሁ እንዲያበቃችሁ፣ በተለያየ
ምክንያት በተፍጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ከቤትና ከቀያችሁ
የተፈናቀላችሁትን እግዚአብሔር ለቤታችሁና ለቀያችሁ ያብቃችሁ፣ በሞት
የተለዩንን ፈጣሪ በገነት ያኑርልን፣ ያዘኑትን ያጽናናልን፣ ሁላችንንም ከወረርሽኝ
በሽታ ይጠብቀን እያልኩና መልካሙን ሁሉ እየተመኘሁ ለሁላችሁም እንኳን
ለ2013 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት
በድጋሚ መልካም ምኞቴን እግልጽላችኋለሁ፡፡
እግዚአብሔር በምሕረቱና በቸርነቱ ይባርከን
አገራችን ኢትዮጵያን በዘውትር ጥበቃው ከክፉ
ሁሉ ይጠብቅልን!
† ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶለካውያን