በጋምቤላ ሃገረስብከት የመንበረ ጵጵስና ርክክብ ተካሄደ።
የሚጠራም የሚልክም እግዚአብሔር ነው
በጋምቤላ የመንበረ ጵጵስና ርክክብ ተካሄደ ጳጳሳት በሰበካው የተለያዩ ቁምስናዎች ተከፋፍለው የሰንበት መሥዋዕተ ቅዳሴ አሳረጉእንደሚታወቀው ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀደም ሲል በሃዋሳ ካቶሊካዊ ሰበካ በእረኝነት ተሰይመው ሲያገለግሉ የነበሩትን ብፁዕ አቡነ ሮቤርቶ በርጋማስኪን የጋምቤላ ሀገረስብከት ጳጳስ አድርገው ሾመዋቸዋል። በዚሁ መሰረት ቅዳሜ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በዕለተ ቅድስት ማርያም ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በመሩት ደማቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ጳጳሳት፣ ካህናት ደናግል ምእመናን የጋምቤላ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ተንኩዋይ ጆ ፣ የክልሉ ምክርቤት እና የካቢኔ ባለስልጣናት ኣእንዲሁም ምእመናን በተገኙበት የሀገረስብከቱ የመንበረ ጵጵስና ርክክብ ተከናውኗል።የሃዋሳ ሀገረስብከትን የሚወክሉ ካህናት እና ደናግል በከፍተኛ ትህትና ብፁዕነታቸውን ለጋምቤላ ሀገረስብከት በማስረከብ ለሃዋሳ ሀገረስብከትም እግዜብሔር መልካም እረኛ እንዲመድብላቸው መላው ሕዝበ እግዝአብሔር እንዲጸልዩላቸው ዐደራ ጭምር ተማጥነዋል፣በሥነሥርዓቱ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን “የሚጠራም የሚልክም እግዜብሔር ነው” ካሉ በኋላ። ብፁዕ አቡነ ሮቤርቶ በጵጵስና መሪ ቃላቸው ላይ “እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉ” በማለት በግልጽ እንዳስቀመጡት ክህነትን ከተቀበሉበት ጊዜ አንስተው እግዚአብሔርን በደስታ ሲያገለግሉ ቆይተው ዛሬ ቤተክርስቲያን በሰጠቻቸው አዲስ አገልግሎት የጋምቤላ ሀገረስብከትን በደስታ ለማገልገል ወደጋምቤላ ሰለመጡ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ የሱስ በቅርቡ ከመካከላችን ተለይተው ወደ ጌታ የሄዱትን የቀድሞ የጋምቤላ ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አንጀሎ ሞረስኪን በማስታወስ ሰለማይረሳው ሕዝብ ወዳጅነታቸው እና ትሁት አገልጋይነታቸው እግዚአብሔር ዋጋቸውን በሰማይ እንደሚከፍላቸው ጽኑ እምነት አለኝ ብለዋል። ክቡር አባ ተስፋዬ የጋምቤላ ካቶሊካዊ ሰበካ ጳጳስ ሳይመደብ በቆየበት ጊዜ ቤተክርስቲያን የጣለችባቸውን ሃላፊነት ተቀብለው ሀገረስብከቱን በማስተዳደር ላበረከቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት አመስግነዋቸዋል። በማስከተልም ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት ቤተክርስቲያን አንዲት አካል ያላት ናት እኛም የእርሷ ልጆች አባባ ብለን የምንጠራው የአንድ ፈጣሪ ልጆች ነን። በክርስቲያኖች መካከል ልዩነት ሊኖር ፈጽሞ አይገባም በማለት በአጽንዖት አስተምረዋል። ክቡር አባ ተስፋዬ ጴጥሮስ በበኩላቸው በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹሕ ወሃ አቅርቦት እና በተለያዩ ዘርፎች የጋምቤላ ካቶሊካዊ ሰበካ እያበረከተች ያለውን ከፍታኛ አስተዋጽዖ ገልጸዋል።የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንትም የካቶሊካዊት ቢተክርስቲያን በክልሉ የምታከናውናቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት ለሕብረተሰቡ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ለመግለጽ ምንም ምስክር አያሻውም። ሕብረተሰባችንን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን የምታከናውን በመሆኑ መንግስት በዚህ ከፈተኛ አጋርነት ይሰማዋል ብለዋል።ብፁዕ አቡነ ሮቤርቶ በርጋማስኪ አዲሱ የጋምቤላ ካቶሊካዊ ሰበካ ጳጳስ “ሁላችንም የእግዜብሔር ልጆች ነን። አብረን መኖር እና ተከባብረን መኖር ይገባናል” ብለዋል። “ዓለማዊው ፖለቲካ ምናልባት ሕብረተሰብን ከሕብረተሰብ ይከፋፍል ይሆናል። የቤተክርስቲያን ፖለቲካ ግን የበሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ፖለቲካ ነው።” ብለዋል። “እግዜብሔርን አባታችን ብለን የምንጠራ ሁላችን እኛ እርስ በእርሳችን ወንድማማቾች ነን። ሁላችን አንድ አባት አለን በዚህ የማይፈርስ እውነት አብረን እንኖራለን” ብለዋል።ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የካቢኔ አባላት ተደራራቢ መርሃግብሮቻቸውን አቻችለው በመካከላችን በመገኘታቸው መስጋናቸን እጅግ የላቀ ነው ብለዋል።እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጳጳሳት በጋምቤላ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች በመጓዝ በሼቦ ቅድስት ማርያም፣ በቦንጋ ቅድስት ባኪታ እና በአቦቦ ተገኝተው መሥዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል። ብፁዕ አቡነ ሮቤርቶ በርጋማስኪ አዲሱ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊክ ካቴድራል የመጀመሪያ የሰንበት መሥዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል።