የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) መልእክት

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) መልእክት
ታኅሣሥ 2018 ዓ.ም
“አትፍሩ፤ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና” (ሉቃስ 2፡10)
ለተወደዳችሁ ካህናት፣ገዳማውያንና ገዳማውያት፣የካቶሊክ ምእመናን፣በውጭ የምትገኙ ካቶሊካውያን በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች፣በኢትዮጵያ የምትገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እና በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሰዎች ሁሉ የስብከተ ገና ቡራኬያችንና ሰላምታችን ይድረሳችሁ፣
ሠላም ለሁላችሁ ይሁን።
1. እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ፣ ከኅዳር 29 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በእምድብር ባደረግነው 59ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ይህንን የአብሮነት ጉዞ (ሲኖዶሳዊ) መልእክት እናስተላልፍላችኋለን። ይህ መልእክት የኢዮቤልዩ ዓመት መዝጊያ እና በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በየሀገረ ስብከቶቻችን የአብሮነት ጉዞ (Synodality) ሰነድ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ መጀመራችንን የምናበስርበት ነው።
2. ጌታ ኢየሱስ በልባችን እንዲወለድ በምንጠባበቅበት በዚህ የስብከተ ገና ወቅት፣ “አትፍሩ” የሚለውን የመልአኩን አጽናኝ ቃል እናስተጋባለን። ይህ ቃል ለእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለእጮኛዋ ዮሴፍ እንዲሁም ከትንሣኤው ጌታ ጋር በተገናኙበት ወቅት ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት እንደተናገረው ሁሉ፤ ዛሬም በተወደደችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ—ለእኛም ዳግመኛ እንደ አዲስ የሚናገረን ቃል ነው። በብዙ መከራዎች—በድህነት፣ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በማህበራዊ መቃወስ እና መከፋፈል—ለምትሰቃይ ሀገር፣ ይህ የመላእክቱ ቃል በጨለማ ውስጥም ቢንሆን መለኮታዊው የክርስቶስ ብርሃን ይዘን ወደ ታደሰ ተስፋና አንድነት እንደሚመራን ያስታውሰናል። በዚህ ቅዱስ የስብከተ ገና ወቅት፣ በንቃትና በተስፋ የምንጠባበቅበት ጊዜ እንደመሆኑ፣ ልባችን መልአኩ ለእረኞች ወደታየበት ሌሊት ያማትራል። የእረኞቹም ዓለም ልክ እንደ እኛው እርግጠኝነት የሌለበትና መከራ የበዛበት ነበር። ከሰማይ የመጣው የመጀመሪያው ቃል “አትፍሩ፤ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና” (ሉቃስ 2፡10) የሚል ነበር።
3. ዛሬም እኛ የእናንተ እረኞች “አትፍሩ” የሚለውን መለኮታዊ መልእክት ለሁላችሁም እናስተጋባለን። ይህንን የምንለው በሀገራችን ያለውን ጥልቅ ስቃይና ፍርሃት ሳናይና ሳንርዳ ቀርተን ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን በእምነት በማረጋገጥ ነው። እርሱ በተጨነቅን ጊዜ ቢሆን እንኳን ተስፋ የማይያስቆርጠን “የሚያበራ ኮከብ” ሆኖ ይመጣል። በዚህ ስብከተ ገና እርሱን የምንጠብቀው በተስፋ መቁረጥ ሳይሆን፣ በአብሮነት (Synodality) ጉዞ— በኅብረት ፣ በተሳትፎ እና በተልዕኮ አብሮ መጓዝን በንቃት ምርጫችን በማድረግ ነው። የተስፋ ዓመት ሲጠናቀቅ፣ የአብሮነት ጉዞ መልእክት እኛን ካህናትን፣ገዳማውያንን፣ ምእመናንን እና በጎ ፈቃድ ያላችሁን ሰዎች ሁሉ በኅብረት እንድንጓዝ ይጋብዘናል። ጌታችን አንድ እንድንሆን በጋበዘን ጥሪ ተነሳስተን፣ በጋራ ጉዟችን ዛሬ ውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ከባድ ተግዳሮቶች መጋፈጥ እንዳለበት እንረዳለን። እንደ ቤተክርስቲያን እረኞች፣ ማኅበረሰባችንን ሊውጡ ባንዣበቡ የመከፋፈል እና የዓመፅ ማዕበሎች ሳንበገር የሰላም፣ የተስፋ እና የእርቅ ድምፅ እንድንሆን ተጠርተናል።
በኢትዮጵያ ያሉብን ተግዳሮቶች፦
ውድ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ስንመለከት የተሸከምነውን ከባድ ሸክም እናያለን። ሀገራችንን ከሚያሰቃዩዋት ሸክሞች መካከል ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ሊጠቃለሉ ይችላሉ፦
4. የኑሮ ውድነት፦ ለብዙ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት ሕይወት ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ሆኗል። የዋጋ ንረቱ መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን እንደ ድሎት አስቆጥሯል። ወላጆች ልጆቻቸው ተርበው ባዶ ሆዳቸውን ሲተኙ በሐዘን ይመለከታሉ። በዚህ ሸክም ምክንያት የቤተሰብ ሕይወት ትስስር እየላላ ነው። ይህም የኢኮኖሚ መዋቅሮች ለሰው ልጅ ክብር ማገልገል አለባቸው የሚለውን እና ለድሆችና ለተጋላጭ ወገኖች ቅድሚያ መስጠት የሚጠይቀውን የካቶሊክ ማኅበራዊ ትምህርት መሠረታዊ መርህ ይቃረናል።
5. የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ፦ ቀጣይነት ያለው ድርቅ እና የአካባቢ መራቆት የመቋቋም አቅማችንን እስከ መጨረሻው እየፈተኑት ነው። ለቀውሱ ጥቂት አስተዋጽኦ ያላቸው ድሆች ከፍተኛውን ዋጋ እየከፈሉ ነው። በረከት በሞላባት ሀገራችን ውስጥ በረሃብ የሚሞቱትን አስቡ። የእግዚአብሔር ፍጥረት ጠባቂዎች እንድንሆን ተጠርተናል (ዘፍጥረት 2፡15)፣ ነገር ግን ዘላቂነት በሌለው መንገድ ውስጥ ተዘፍቀናል። ይህም ሥነ-ምህዳዊ ንስሐ (ecological conversion) እንድናደርግ እና በጋራ እርምጃ እንድንወስድ ያሳስበናል። በ”ላውዳቶ ሲ” (Laudato Si) ላይ እንደተገለጸው፡ ስህተቶቻችንን እና ኃጢአታችንን አምነን በመቀበል፣ ለልባዊ ንስሐ እና ለውጥ የሚገፋፋ የልብ እና የሐሳብ ለውጥ ያስፈልገናል። (LS 218)
6. የባህል መቃወስ እና መከፋፈል፦ የጎሳ ግጭቶች፣ የዘር ጥላቻ እና የመከፋፈል አስተሳሰቦች የተቀደሰውን ብሔራዊ ትስስራችንን ሊበጣጥሱት እየሞከሩ ነው። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ የጋራ ማንነታችንን አደጋ ላይ እየጣለ እና የሚያስተሳስረንን ትስስር እያዳከመ ነው። በዲጂታላይዜሽን የተቀረፀው አዲሱ ባህል የቆዩ እሴቶቻችንን እያጠፋ ነው። ዘመን አመጣሹን ባህል ያለ በቂ ማስተዋልና ሂሳዊ አስተሳሰብ እየተቀበልን ያለ ይመስላል። በማኅበራዊ ሚዲያ እየተጋነነ የመጣው አደገኛ “እኛ እና እነርሱ” የሚል መንፈስ የጋራ እሴቶቻችንን እያበላሸና ወጣቶቻችንን እያደናገረ ነው። የእያንዳንዱ ሰው ደህንነት ከሌላው ጋር የተቆራኘ መሆኑን የሚገልጸውን የጋራ ጥቅም ስሜት የማጣት አደጋ ተጋርጦብናል።
7. ማለቂያ የሌለው ግጭት፦ ከቅርብ ጊዜው የእርስ በርስ ጦርነት ትልቅ ቁስል ጀምሮ እስከ አሁናዊው አካባቢያዊ ግጭቶች ድረስ ሀገራችን በሥቃይ ተውጣለች። ሰላምና ደህንነት ምኞት ሆነዋል። በሃይማኖት፣ በዘር ወይም በፖለቲካ ላይ የተመሰረቱ ትርጉም የለሽ ግጭቶች በበቀል እና በጥፋት አዙሪት ውስጥ ዘፍቀውናል። ይህም የሰላም መሳሪያዎች እንድንሆን ከሚጠራው የወንጌል ቃል (ማቴዎስ 5፡9) እና ለፍትህ እና ለእርቅ ከሚቆመው የቤተክርስቲያን አስተምሮ ጋር በቀጥታ የሚቃረን ተግባር ነው። ክቅርብ ዓመታት ጀምሮ ሀገራችንን እያናወዘ ያለው የስላም እጦት ሁከት በእጅጉ ያሳስበናል። የጦርነት ድምፅ በልባችንና በቤታችን እያስተጋባ ግራ በመጋባት ስሜት ውስጥ ነው ያለነው። የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆነ የማኅበራዊ ግጭቶች ብዙዎችን ለፍርሃትና ለጭንቀት ዳርገዋል። በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ያለው የደህንነት እና የሰላም እጦት ፈጽሞ ሊታለፍ የማይችል ከባድ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በዚህም ምክንያት ቤተሰቦች ተበታትነዋል፣ ማኅበረሰባዊ እሴቶች ተሰባብረዋል፣ በአንድ ወቅት እንታወቅበት የነበረው የአንድነት መንፈስም ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምታስተምረን ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ የፍትህ መኖር እና የሰው ልጅ ክብር ማበብ መሆኑን ነው። ሀገራችንን እያሰቃዩ ያሉት ግጭቶች ላይ ስናሰላስል፡ “መቼ ነው የሚበቃን? መቼ ነው ከግጭት አዙሪት ተመልሰን ወደ መፈወስና መልሶ ግንባታ የምንዞረው?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። እነዚህን ችግሮች በግልጽ መጋፈጥ፣ ስለ ሀገራችን ሁኔታ እውነቱን መናገር እና በሰላም ላይ ለተመሰረተ መጻኢ እድል መሟገት የሁላችን ቅዱስ ተግባር መሆን አለበት። የቀጠለው ግጭት የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ አስከፊ ነው። በኢኮኖሚ ረገድ ሀገራችን እየተጎዳች ነው፤ ቤተሰቦች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት እየታገሉ ነው፣ እንዲሁም የትምህርትና የሥራ ዕድሎች በእጅጉ እየቀነሱ መጥተዋል። ዜጎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ነው፣ ሕፃናትና አረጋውያንም ለዚህ ግጭት ከፍተኛውን ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። በባህል ረገድም፣ ልዩነቶች እየሰፉና አለመተማመን ሥር እየሰደደ በመምጣቱ ውብ የሆነው የብዝአነት እሴታችን አደጋ ውስጥ ገብቷል። በማኅበራዊ ደረጃም፣ ብዙ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች (IDPs) በመሆን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ እናያለን። ከዚህም አልፎ ሃገራቸውን ትተው በመሰደድ በብዙ ችግርና አደጋ ውስጥ የወደቁ ብዙሃን ናቸው። በሰለጠኑ ሀገራት የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት በዲያስፖራ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያን በፍርሃት እና በሰቀቀን ዉስጥ ህይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ። በጦርነት የሚደርሰው ስቃይ ከጦር ሜዳው ያለፈ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ይህ ስቃይ እስከ ማኅበረሰባችን መሠረት ድረስ ዘልቆ በመግባት ልጆቻችንን፣ አረጋውያንን እና የወደፊት ሕይወታችንን እየነካ ነው። እንደ ቤተክርስቲያን፣ በእንዲህ ያለ ስቃይ ፊት ዝም ማለት አንችልም። ይልቁንም የሰላም መሣሪያ፣ ድምፅ ለሌላቸው ተሟጋች እና ለእርቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እንድንሰራ ተጠርተናል።
8.የተግባቦት እንቅፋት፦ ትልቁ ውድቀታችን የመወያየት አቅም ማጣታችን ሊሆን ይችላል። “እኔ ካላሸነፍኩ” የሚል አስተሳሰብ እና ራስ ወዳድነት እርስ በርስ የመደማመጥ ባህልን ተክተዋል። ከቤተሰብ እስከ ፖለቲካ ልሂቃን ድረስ፣ እርስ በርስ መደማመጥ አቅቶን እንደ “ባቢሎን” ግራ መጋባት ውስጥ እንገኛለን። በቋንቋ፣ በፖለቲካ እይታ እና በሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ምክንያት የመጡ እንቅፋቶች ግንኙነታችንን ተቆጣጥረውታል። ሁላችንም ወንድማማቾች ነን (Fratelli TuF) በሚለው መልእክት ላይ እንድተገለጠው “እውነተኛ ማኅበራዊ ውይይት የሌላውን ሰው አመለካከት ማክበርንና ተገቢ የሆኑ አሳቦችን ሊይዝ እንደሚችል አምኖ መቀበልን ይጠይቃል” (#203)።
9. ምንም እንኳ ከባድ ችግሮች ቢኖሩም፣ ሀገራችን በብዙ ዘርፎች አስደናቂ የሆነ የጥንካሬ እና የጽናት መንፈስ አሳይታለች። ለወደፊት የኢኮኖሚ እድገት ተጨባጭ መሠረት የጣሉ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች ፣ የግብርና ምርታማነት እና የኤክስፖርት ምርቶች ዓይነት መጨመር፣የዲጂታል ሽግግር ከሀገር በቀል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ (Fintech) እድገት ጋር ተዳምሮ፣ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም መነቃቃት እና የሰላም እንቅስቃሴዎች፣ ንቁ የግል ዘርፍ ተሳትፎ፣ የ”አረንጓዴ አሻራ” ስራዎች በኢኮኖሚያዊ እራስን የመቻል ጥረቶች ጋር፣ ሀገር በቀል መፍትሄዎች እና የሕዝብ ቁጥር ስብጥር ምቹነት (Demographic dividend) ሀገራችንን ለመለወጥ ተስፋ የሚሰጡ እና እንደ መሪ ፍልስፍና የሚያገለግሉ ዋና ዋና አዎንታዊ ገጽታዎች ናቸው።
በዚህ በፍርሃት ወቅት ሊኖረን የሚገባው ሲኖዶሳዊ ጉዞ
10. የወንጌል መልእክት፣ በተለይም “አትፍሩ” የሚለውን አዝማች፣ በታሪካችንና በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያስተጋባል። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ “ጋውዲየም ኤት ስፔስ” (Gaudium et Spes) በመከራ ውስጥም ቢሆን “ክርስቶስ ዓለምን አሸንፏል” (ዮሐንስ 16፡33) በማለት ያስታውሰናል፤ ይህም የሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) ጥሪ አብሮነትን ይዘን በመጓዝ በእርሱ ድል እንድንካፈል ጥሪ ያቀርብልናል። በ“ሴንቴሲመስ አኑስ” (Centesimus Annus) ውስጥ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስለ ሰው ልጅ ክብር እና በክርስቶስ ተልዕኮ ውስጥ መካፈል ስላለው አስፈላጊነት አንፀባርቀዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ሁላችንም ወንድማማቾች ነን (Fratelli Tutti) የሚለው የር.ሊ.ጳ. አቡነ ፍራንቺስኮስ መልእክት በሀገራችን ውስጥ ያሉ መከፋፈሎችን ለመፈወስ እጅግ አስፈላጊ ወደሆኑት የውይይት፣ የይቅርታ እና የወንድማማችነት ባህል ይጋብዘናል። የሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን የመጨረሻው ሰነድ እውነተኛ ኅብረት መደማመጥን፣ ግልጽነትን እና የጋራ ኃላፊነትን እንደሚጠይቅ ያጎላል። ቫዴሜኩም (Vademecum) የተባለው መመሪያም ይህንን ጉዞ ደረጃ በደረጃ እንዴት እንደምንጓዝ የሚመራን ሲሆን፣ ሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) ሂደት ብቻ ሳይሆን የሕይወት መንገድ— ማኅበረሰቦችንና ነፍሳትን የሚለውጥ የማያቋርጥ አብሮነት መሆኑን ያሳስባል። በቅርቡ የተጠናቀቀው ዓለም አቀፍ የሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) ሲኖዶስ እና መሪ ሰነዱ፣ ቤተክርስቲያን ለሰው ልጆች ሁሉ ሕያው የኅብረት ምልክት እንድትሆን የተጠራች መሆኗን ያስታውሱናል። የአብሮነት ጉዞ (Synodality) “ቤተክርስቲያን እንድትጓዝበት የተጠራችበት መንገድ ነው… ይህም እያንዳንዱ ሰው በጋራ የመደማመጥ እና የማስተዋል (discernment) ጉዞ ውስጥ እንዲሳተፍ ያደርጋል” (ሲኖዶስ ቫዴሜኩም)። ይህ የቤተክርስቲያን ልምምድ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም እንደ ሀገር ለገጠሙን ጥልቅ ቀውሶች ትንቢታዊ ምስክርነት እና ተጨባጭ መልስ ነው። ከፍተኛ ፍርሃት ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ አብሮ መጓዝ የሚከፋፍሉ እና የሚያፈርሱ ኃይሎችን ሁሉ መቋቋም የሚያስችል ተግባር ነው።
11. የተወደዳችሁ ካህናቶች፣ ገዳማውያንና ገዳማውያት፣ ካቴኪስቶች እና ምእመናን፤ በኅብረት (communion)፣ በተሳትፎ (participation) እና በተልዕኮ (mission) ላይ የተመሠረተች ይበልጥ ‘ሲኖዳዊት ቤተክርስቲያን’ እንድንሆን እንጋብዛችኋለን። የሲኖዳዊውን መንገድ በተግባር ላይ ለማዋል፣ የሚከተሉት ማዕቀፎች በየሃገረ ስብከቶቻችሁ ውስጥ የማያቋርጥ የልብ ለውጥ (conversion) እና ተግባር እንዲኖራችሁ ይረዷችኋል፣
- የጉዞ ጓደኝነት፦ ሁሉም የቤተክርስቲያን አባላት በጋራ መንፈሳዊ ጉዞ (pilgrimage) ላይ መሆናቸውን ለመቀበል አትፍሩ፤ ይህም እርስ በርስ መደጋገፍንና አብሮነትን የሚያበረታታ ነው። ልንሆን ወደምንፈልጋት ቤተክርስቲያን በምናደርገው ጉዞ ማንም ሰው መገለል ወይም ወደኋላ መቅረት የለበትም።
- ኅብረት፣ መገንባትና መደማመጥ፦ እርስ በርስ ፣ በተለይም ዳር ቆመው ከሚገኙት ጋር – በጥልቀት ለመደማመጥ ጥረት ማድረግን አትፍሩ። ክርስቶስ የእኛን ሥቃይ እንደሚሰማ ሁሉ፣ እኛም የተገለሉትን፣ ወጣቶችን እንዲሁም በግጭትና በኢኮኖሚ ችግር የሚሰቃዩትን ድምፅ መስማት ይኖርብናል። ይህ ንቁ መደማመጥ መተማመንንና አንድነትን ይፈጥራል፤ እንዲሁም ፍርሃትን በትብብር ለመቋቋም ይረዳል።
- ሐሳብን በነፃነት መግለጽ (Speaking Out) ፦ ሁሉም የተጠመቁ ምእመናን ልምዶቻቸውንና የሚያሳስቧቸውን ጉዳዮች በታማኝነት፣ በልበ ሙሉነት እና በጥንቃቄ እንዲናገሩ የሚያበረታታ ከባቢ ለመፍጠር አትፍሩ። ይህም በክስና በወቀሳ መልክ ሳይሆን፣ በወንድማማችነት እርማት (fraternal correction) መንፈስ ሊሆን ይገባል።
- የሥርዓተ አምልኮ ሕይወት (Celebrating)፦ የቤተክርስቲያን የሲኖዶሳዊ ጉዞ ምንጭና ማማ የሆነውን የሥርዓተ አምልኮ ሕይወትና የጋራ ጸሎት አስፈላጊነትን እውቅና ለመስጠት አትፍሩ፤ ይህ ሲሆን ነው በአንድነት ውስጥ ያለ ልዩነት (unity in diversity) በተግባር የሚገለጠው።
- ለተልዕኮ የጋራ ኃላፊነት (Co-responsibility in the Mission)፦ ሁሉም የቤተክርስቲያን አባላት በጥምቀታቸው አማካኝነት ለቤተክርስቲያን የወንጌል ስርጭትና አገልግሎት ተልዕኮ ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚገልጸውን ግንዛቤ ለማሳደግ አትፍሩ። በየቁምስናችሁ ተልዕኮ ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ አትፍሩ ወይም ወደኋላ አትበሉ። በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ የካቶሊክ እምነትንና እሴቶችን ለማስፋፋት በንቃት ተሳተፉ! በሁሉም ተቋሞቻችን ውስጥ፣ የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ እድገት (Integral human development) የቤተክርስቲያናችን ተልዕኮና ራዕይ አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ምንም ዓይነት የዘር፣ የሃይማኖት ወይም የማንነት ልዩነት ሳይደረግ መላውን የሰው ልጅ የሚጠቅም መሆን አለበት።
- በቤተክርስቲያንና በማኅብረሰቡ ውስጥ ውይይት ማድረግ፦ ሰዋዊ አገናኝ ድልድዮችን ለመገንባትና ወቅታዊ ፈተናዎችን ለመፍታት በቤተክርስቲያን ውስጥና ከማኅበረሰብ ጋር—የተለያዩ ባህሎችን፣ ሃይማኖቶችንና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ—የሚደረግን ውይይት ለማበረታታት አትፍሩ። በቤተሰባችሁ፣ በጎረቤቶቻችሁ፣ በየቁምስናቹ፣ በየአህጉረ ስብከቶቻችሁና ውስጥ የውይይት ባህልን ለማሳደግ አትፍሩ።
- ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላችሁ ግንኙነት፦ ወደ አንድነት የሚወስደውን መንገድ ለማጠናከር፣ የቤተክርስቲያናት አንድነትን (ecumenism) በንቃት ለመፈለግ፣ በሌሎች አብያት ክርስቲያናት ያሉ እሴቶችን ለመስማትና ከእነሱም ለመማር አትፍሩ። v ሥልጣን እና ተሳትፎ፦ የቤተክርስቲያንን መዋቅር (hierarchical structure) በጠበቀ መልኩ፣ የሁሉንም አባላት ተሳትፎና የጋራ ኃላፊነት የሚያመቻች መዋቅራዊ ሥርዓት እንዴት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆን እንደገና ለመገምገም አትፍሩ።
- በማስተዋል ማጤን (Discernment) እና ውሳኔ መስጠት፦ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመለየት እና የማኅበረሰቡን የጋራ ጉዞ የሚያንፀባርቁ ውሳኔዎችን ለመወሰን፣ በጸሎትና በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ የጋራ ማስተዋል እና የማሰላሰል (discernment) ሂደቶችን ተግባራዊ ለማድረግ አትፍሩ።
- ራሳችንን በሲኖዶሳዊ ጉዞ(Synodality) ማነጽ፦ የሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) መርሆችና አሠራሮች ቤተክርስቲያን በሁሉም ደረጃዎች የምትመራበት መደበኛ መንገድ እንዲሆኑ፣ ለቀጣይ ሥልጠናና የመዋቅሮች መታደስ (እንደ ቁምስና የፋይናንስ ምክር ቤቶች ያሉ) ራስን ለመስጠት አትፍሩ።
የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ለሲኖዶሳዊ ጉዞ መልካም አርዓያችን ናት
12. በቀላልና በአጭር አገላለጽ፣ ሲኖዶሳዊ ጉዞ (Synodality) ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ብርሃን እያበራች ከእያንዳንዱ ሰው ጋር አብራ ለመጓዝ እንድትችል፤ ይበልጥ አሳታፊና ተልዕኮ ተኮር የሚያደርጋት የመንፈሳዊ መታደስና የመዋቅራዊ ለውጥ መንገድ ነው ። በሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፤ የሲኖዶሳዊት፣ ተልዕኮ ተኮር እና መሐሪ ቤተክርስቲያን መገለጫዎች በክርስቶስ፣ በቤተክርስቲያን እና በሁላችን እናት በድንግል ማርያም ላይ በሙሉ ብርሃን ሲያንጸባርቅ እናያለን። እሷ የምታዳምጥ፣ የምትጸልይ፣ የምታስተነትን፣ የምትወያይ፣ አብራ የምትጓዝ፣ የምታጤንና የምታስተውል፣ ነገሮችን በጥበብ የምታስተውል፣ ነገሮችን በጥበብ የምታስተነተን፣ የምትወስን እና ተግባራዊ የምታደርግ ቤተክርስቲያን አምሳያ ናት። ከድንግል ማርያም በጥንቃቄና በአስተውሎት የማድመጥ ጥበብን፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ትኩረት መስጠትን፣ ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝን እና የድሆችን እሮሮ ለመስማትና ዝግጁ መሆንና አብሮ መጓዝን እንማራለን። እንዲሁም ችግረኞችን ለመርዳት የሚነሳሳና እና በመንፈስ ተነሳስቶ ሐሴት የሚያደርገውን የምስጋና ቅኔ ከእሷ እንማራለን። (MC,28)(#29).
ስለዚህም “አትፍሩ፤ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና” የሚለውን ቃል በጥሞና አሰላስሉ። የስብከተ ገና ተስፋ ልባችሁንና ቤታችሁን ይሙላው። መልካም የልደት ክብረ በዓል ያድርግላችሁ። የሚያበራው ኮከብ ኢየሱስ እየመጣ ነውና፣ የልደቱ ጸጋ ሁላችንንም በብርታት እና ያለ ፍርሃት እንድንቆም ይርዳን። የእናንተው እረኞች
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት
ታኅሣሥ 2018 ዓ.ም
