በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ለሀገረስብከት ካህናት ገቢ ማስገኛ የሚሆን “ሰላም” የመኖሪያ መንደር ቡራኬ ተካሄደ።

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተገነባው “ሰላም” የመኖሪያ መንደር ቡራኬ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ተካሄደ። በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነባው ባለ 8 ወለል የመኖሪያ መንደር ላለፉት 7 ዓመታት በግንባታ ላይ የቆየ ሲሆን 85 በመቶ የሚሆነው የግንባታ ሂደት መጠናቀቁ ተገልጿል።

“ሰላም” የመኖሪያ መንደር በጀርመን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሮተንበርግ ስቱትጋርት ሀገረስብከት፣ በቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንቼስኮስ እና በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ አጋርነት በጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተባባሪነት ተገንብቷል።

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ፕሬዝደንት ባስተላለፉት መልዕክት “ይህ ተቋም እውነተኛ የሐዋርያዊ ድጋፍ እና ወንድማማችነት የታየበት፤ካቶሊካውያንን በያሉበት በመድረስ ለሚያገለግሉ የሀገርስብከት ካህናት መሰረታዊ ፍላጎችን ለሟሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችንን በልዩ መልኩ ያጠናክራል” ብለዋል። “በተጨማሪም የቤተክርስቲያን ወደፊት በተለይም የውጪ ድጋፍን በመቀነስ ራሷን የምትችልበት አንዱ አማራጭ መሆኑ እና በሐዋሪያዊ ዘርፍም የሚያነቃቃ ትልቅ ራዕይ ያለው ተቋም ነው” ብለዋል።

የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ የሆኑት ክቡር አባ ከተማ ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው “ህንጻው ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን 39 የመኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ የሚውሉ ሱቆች፣ የስብሰባ አዳራሾች እና ሰፊ የመኪና ማቆሚያ አለው” ብለዋል። እንዲሁም ቤተክርስትያን ይህን የገቢ ማስገኛ ተቋም በኢኮኖሚ ዘርፍ በዘላቂነት ራሷን ለመቻል ከምታከናውናቸው ሥራዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። 

የእመቤታችን የኢትዮጵያ ካህናት ማህበር ፕሬዝደንት ክቡር አባ ፍስሃ ታፈሰ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት የካህናትን ህይወት እና ማህበራዊ ደህንነት ለማጠናከር ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። በተለይም ይህ የካህናትን ወንድማማችነት የሚያጠናክር እና ለወደፊትም ካህናትን መሰረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት አብሮነትን የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።

በመርሃግብሩ የቅድስት መንበር ተወካይ በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት፣ በጀርመን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሮተንበርግ ስቱትጋርት ሀገረስብከት ጳጳስ እና የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰበካ ካህናት፣ የጠቅላይ ጽ/ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

Saint of the day

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300