በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአሜሪካ ጳጳሳት ጉባኤ የማህበራዊ ልማት ጽ/ቤት (CRS) ፕሬዝደንት በኢትዮጵያ ጉብኝት አደረጉ።

የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ ጳጳሳት ጉባኤ የማህበራዊ ልማት ጽ/ቤት ፕሬዝደንት ሾን ካላሃን በኢትዮጵያ በመገኝት ላለፉት 10 ቀናት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ጉብኝት አድርገዋል።

ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ተቋሙ ባዘጋጀው መርሃግብር የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ ፕሬዝደንት ሾን ካላሃን፣ የተቋሙ የምስራቅ እና ምዕራብ አፍሪካ ሥራ አስፈፃሚ ማት ዴቪስ፣ የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመዴ ዘውዴ፣ የእማሆይ ተሬዛ ገዳማውያት፣ የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽኃፊ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት፣ አጋር ተቋማት እና የልማት ጽ/ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በስብሰባውም ተቋሙ ከስድስት አስርት አመታት በላይ በዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ አገልግሎት ላደረገው አስተዋፅዖ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አመስግናለች። በቀጣይም በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ለማሟላት እና በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ አቅጣጭ የሚፈጠረውን የሰላም ዕጦት ለመቀነስ ከምንግዜውም በጋራ ለመስራት ተወያይተዋል።

በአሜሪካ ጳጳሳት ጉባኤ በኩልም አለም ዓቀፍ ያለውን ለውጥ እና የድጋፍ እጥረት ተቋሙ ላይ የፈጠረውን ጫና የገለፁት ፕሬዝደንት ሻን ካላሃን በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ የተመለከቱት ግን ለበርካታ የተቋሙ አጋሮች ህያው ምስክር መሆን የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመዴ በበኩላቸው የፕሬዝደንቱ ጉብኝት በዋነኝነት የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት በአለም ዓቀፍ ደረጃ ያለበትን ሁኔታ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተጨማሪም ከአሜሪካ መንግስት በመቀጠል አለም አቀፍ የተቋሙ አጋሮችን ለማበረታታት ይህ ጉብኝት የሚኖረውን ከፍተኛ ሚና ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስን በመወከል በመዝጊያ መርሃግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የአሜሪካ ጳጳሳት ጉባኤ በኢትዮጵያ ላለፉት አመታት በነበሩ ሰብዓዊም ሆነ ተፈጥሯዊ ቀውሶች ከጎን በመሆናቸው አመስግነዋል። በአሁኑ ወቅትም ባለው ለውጥ በእግዚአብሔር እርዳታ የሚደረገው ድጋፍ የማይቋረጥ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ካቶሊካውያንም በውጪ ድጋፍ ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የሚያነቃቃ ጥሪ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ መሪነት ፕሬዝደንት ሻን ካላሃን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝደንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አድርገዋል። በቆይታቸውም ክቡር ፕሬዝደንት አምባሳደር ታዬ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለይም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ለሰው ልጆች ሁሉ ለምታደርገው አገልግሎት እንዲሁም የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች በመድረስ በማድረግ ላይ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግስት ያመሰግናል ብለዋል።

ፕሬዝደንት ሾን በበኩላቸው ተቋሙ በኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አመታት በጽናት ህብረተሰቡን ማገልገል እንዲችል አስተዋጽዖ ላደረጉት ለኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት እና በየክልሉ ለሚገኙ አስተዳደሮች እና ማህበረሰብ፣ ለጠቅላላ የተቋሙ ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በጉብኝታቸውም በሆሳዕና፣ በእምድብር፣ በመቀሌ እንዲሁም በአዲስ አበባ በርካታ ፕሮጀክቶችን መመልከታቸውን እና ይህም እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት (CRS) እ.ኤ.አ. 2024 ብቻ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በ134 ሀገራት 200 ሚሊዮን ሰዎች ጋር በመድረስ ድጋፍ ማድረግ ችሏል። በኢትዮጵያ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት በመመደብ ከ7.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እና ሌሎች ዘርፈብዙ አገልግሎት መስጠት ችሏል።

Saint of the day

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300