ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ የተላለፈ  የእርቅና የሰላም ጥሪ

                       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።

        “ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።” (ማቴዎስ 5፥9)

በክርስቶስ ፍቅር ለተወደዳችሁ ልጆቻችን ካቶሊካውያን ምዕመናንና፣ በአገራችንና በዓለም ዙሪያ ለምትገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች፤ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር፣ ሰላምና ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአገራችን በትግራይ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም አካባቢዎች ባለው ጦርነት ጥልቅ ኃዘኗን ትገልጻለች። የጦርነት መንገድ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ ያባብሳል፤ እንዲሁም ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት መጥፋትን፣ አሰቃቂ የንብረት ውድመትንና በትውልዶች መካከል የሚኖርን ቂምና በቀልን ጥሎ ያልፋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመስከረም 20 ቀን በአገራችን ኢትዮጵያ ስላለው የሰላም ጥማት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክታቸው “ጦርነትና ግጭት እንደገና በተቀሰቀሰባቸው በትግራይና ጎረቤት በሆኑት በአፋርና በአማራ ክልሎች ያለውን ሁኔታ በቅርብ እከታተላለሁ…….. ሁሉም ወገኖች የውይይትን መንገድ እንዲመርጡ ልባዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ… የጦርነት መንገድ በፍጹም ችግሮችን አይፈታም፤ ይልቁንም የሞት፣ የንብረት ውድመት እና የቂም በቀል ጠባሳን ጥሎ ያልፋል……. ዘላቂ ሰላምን እውን ማድረግ የሚቻለው በእውነተኛና ታማኝ ውይይት ብቻ ነው……….።” በማለት አባታዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ጥሪ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ፣ በመካከላችን አንዳንድ ልዩነት ቢኖሩም፣ የሌላውን ሕይወት እንደ የራሳችን ሕይወት፣ የሌላውን ሥቃይ እንደ የራሳችን ሥቃይ እንድንመለከት ይማጸናል፤ ምክንያቱም የአገራችን የኢትዮጵያ ሰላም የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ችግሮች በውይይት ተፈትተው ግጭቶች ባይኖሩ የሁላችንም ምኞት ነው፤ ነገር ግን እንደሚታወቀው፣ በግጭት ወቅትና መካከል በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና ታማሚዎች ይበልጥ ተጎጂ ይሆናሉ ። ይህ ሁኔታ እንዳይከሰትና የሁሉም ሕይወት እንዲጠበቅ ጥሪያችንን እያቀረብን በጸሎትም እንተጋለን። እውነትን፣ ፍትሕን፣ ይቅርታንና እርቅን መሠረት ያደረገ ዘላቂ ሰላም ለሁሉም ወገኖችና ለመላው ሕዝባችን የሚበጅ፣ ከወንጌል መንፈስም ጋር የሚስማማ መንገድ እንዲሁም ብቸኛው እግዚአብሔር የሚወደው አማራጭ መሆኑን በጽኑ ያስገነዝባል።

ከሁሉ በላይ፣ የወንድማማችነትንና የእህትማማችነትን መንፈስ በማደስ ለአገራችንና ለህዝባችን ዘላቂ ሰላም ሲባል ሁሉም ወገን ለይቅርታና ለእርቅ ልቡን እንዲከፍት ቤተክርስቲያናችን ምክሯን ታስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ዛሬ መስከረም 21 ቀን፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በሚከበርበት ከዚህ የተቀደሰ ዕለት ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2019 ዓ.ም. (Oct.1- Oct.31, 2026) በዓለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያናችን ትውፊት መሰረት የማሪያም ወር በመሆኑ በተለየ ሁኔታ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚደረግበት ነው፤ እንዲሁም በሀገራችን የቤተክርቲያን አስተምህሮ ከመስከረም 26 እስከ ሕዳር 5 ቀን 2019 ዓ. ም. ያለው ዘመነ ጽጌ (ጾመ ቁስቋም) ወቅት ስለሰላም በምናደርገው ጸሎት መበርታት ስላለብን፣ መላው ካቶሊካውያን ምዕመናንና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ በጾምና በጸሎት እንዲበረቱ ያሳስባል። በተጨማሪም መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም. የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ክብረ በዓል በተለይም የ800ኛ ዓመት ዝክረ ሞት መታሰቢያ የሚከበርበትን ዕለት በማሰብ በየቀኑ በግላችንና በየቁምስናው፣ በየእሁዱ በመስዋዕተ ቅዳሴ መጨረሻ ላይ የቅዱስ ፍራንቺስኮስ የሰላም ጸሎት የሆነውን፣ ጌታ ሆይ የሰላም መሳሪያ እንድሆን አድርገኝ፤ ጥል ባለበት ፍቅር፤…….የሚለውን ጸሎት እንድናደርግ ጥሪ ያቀርባል።

በዚህም የጸሎት ጥሪ ለአገራችን አስተማማኝ ሰላምና የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ፍቅር በሙላት ይወርድ ዘንድ ዘወትር ሳይሰለቹ በመንፈሳዊ ተጋድሎና በጸሎት በመጽናት፣ በየፊናችን ስለሰላም መስራት እንደሚያስፈልግ በታላቅ ትህትና እናሳስባለን።

የአምላካችን ሰላም፣ ፍቅርና ምሕረት በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ ይሁን!

መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ


Leave a Reply

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300