በሐረር ሀገረስብከት በሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

በሐረር ሀገረስብከት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ አማካይነት ከየካቲት 5 እስከ የካቲት 6/2018 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ቀናት የቆየ ሥልጠና በሀገረስብከቱ ውስጥ ለሚያገለግሉ ካህናት እና ደናግል በድሬዳዋ ቅዱስ አውግስጢኖስ ቁምስና ግቢ በሚገኘው አዳራሽ ውስጥ ተሰጥቷል። የሥልጠናው ዋና ርዕስ “ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን” የሚል ሲሆን ሥልጠናው በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኮረ ነበር።

ሥልጠናውን በመሥዋዕተ ቅዳሴ እና በቡራኬ የከፈቱት የሐረር ሀገረስብከት ጳጳስ አቡነ አንጀሎ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸውም “የሥልጠናው ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትሆን ዘንድ እንዴት እንሥራ፤ ምን እናድርግ” የሚል እንደሆነ ገልጸው የተለያየ ምክርና ሀሳብ ሰጥተዋል። በማከልም አሁን የምንገኝበት ጊዜ በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ውይይት ከሚደረግበት ደረጃ ወጥተን ወደ ተግባር መሸጋገር እንደሚያስፈልግና ለሥራውም ሁሉም በመንፈሳዊነትና በተነሣሽነት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የሁለቱን ቀናት ሥልጠና የሰጡት ክቡር አባ ምሥራቅ ጥዩ ስለ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ምንነት እና በሲኖዶሱ ዙሪያ ተዘጋጅቶ ስለቀረበው “የመጨረሻው ሰነድ” አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊት የምትሆንበትን መንገድ እና ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊት እንድትሆን እያንዳንዱ የተጠመቀ ምእመን መወጣት ስለሚገባው ኃላፊነት በዝርዝር አብራርተዋል።


ተሳታፊዎችም ስለ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን አመለካከት ከማደበርም አልፎ በጋራና በቡድን ተወያይተዋል፤ የሀረር ሀገረስብከት ወቅታዊ ሁኔታና ዓውድ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ገንቢ ሀሳቦችንና አስተያየቶች ሰጥተዋል፤ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊት ትሆን ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የሀገረስብከቱ ሐዋርያዊ ሥራ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ዐማኑኤል ባሳ ሥልጠናውን ለሰጡት ለክቡር አባ ምሥራቅ እና ሥልጠናው እንዲዘጋጅ ለተባበሩ ሁሉ ካመሰገኑ በኋላ፤ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊት እንድትሆን ለውጡ ከራስ እንደሚጀምር፣ የሁሉም ሰው ትብብርና አስተዋጽኦ እንደሚጠይቅና በቀናነት፣ በቆራጥነት እና ራስን በመስጠት ማገልገል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የሀገረስብከቱ ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አባ እንድርያስ የሥልጠናውን መርሐ ግብር በጸሎት ዘግተዋል፡፡

ጥንቅሩ የሐረር ሀገረስብከት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ ነው፡፡  


Leave a Reply

Saint of the day

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300