የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የወጣቶች ቢሮ ከክኔዋ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ወጣት ካቶሊካውያን የበጎ ፍቃደኞች ፕሮግራም በአዲግራት ሀገረስብከት በይፋ አስጀመረ።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የወጣቶች ቢሮ ከቅርብ ምስራቅ ካቶሊክ የበጎአድራጎት ማህበር በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ወጣት ካቶሊካውያን የበጎ ፍቃደኞች ፕሮግራም በአዲግራት ሀገረስብከት በይፋ አስጀመረ።
በወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ በማተኮር የሚሰራው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የወጣቶች ቢሮ በጎ ፍቃደኛ ካቶሊክ ወጣቶች ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ ከቅርብ ምስራቅ ካቶሊክ የበጎአድራጎት ማህበር (ክኔዋ) ኢትዮጵያ በመባል ከሚጠራው አጋር ድርጅት ጋር በመተባባር በመጀመሪያ ዙር አምስት ሀገረስብከቶችን በማሳተፍ በብሔራዊ ጽ/ቤት አሰተባባሪነት ተጀምሯል።

ፕሮጀክቱ በተለያዩ ሰበካዎች የሚገኙ ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው የሥራ ዕድል እስከሚያገኙ ባለበት ወቅት የአቅም ግንባታ፣ እና የክህሎት ስልጠና በማመቻቸት ወጣቶች የሥራውን አለም በተሻለ ዝግጅት እንዲቀላቀሉ የሚያግዝ እና የሚያመቻች መሆኑን ተገልጿል። በዚህ ፕሮጀክት የሚሳተፉ ወጣቶች በሥልጠናው ሂደት የቤተክርስቲያን ተቋማት ውስጥ በበጎ ፍቃድ እንዲያገለግሉም መመቻቸቱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ሪት የምስራች አሰፋ ገልጻለች።
በአዲግራት ሀገረስብከት በተካሄደው ሥልጠና የሰበካው የሐዋርያዊ ሥራዎች አስተባባሪ ክቡር አባ ተስፋዬ ኃይለስላሴ በመገኘት መርሃግብሩን በጸሎት እና መልዕክት አስጀምረዋል። ሥልጠናው የወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ያተኮረ ሲሆን በወጣቶች መንፈሳዊ ህይወት ጥንካሬ እንዲረዳ ከቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ “ሁላችንም ለቅድስና ተጠርተናል” ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ አስተንትኖ በክቡር አባ ሙሴ ዶሪ (ዶ/ር) ተሰጥቷል። በመቀጠልም የህይወት ክህሎት ስልጠና በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የቅዱስ ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋም ተወካዮች ተሰጥቷል።

