“በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ሰብዓዊነትን የማስጠበቅ ኃላፊነት” በሚል መሪ ቃል የ ሀገረስብከት ጽ/ቤት የማህበራዊ ተግባቦት ባለሙያዎች ስልጠና ተካሄደ

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት አዘጋጅነት ከህዳር 16 እስከ 17 ቀን 2019 ዓ.ም. በየሀገረስብከት ጽ/ቤቶች በሚዲያ ዘርፍ ለሚያገለግሉ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የጳጳሳት ጉባኤ የወጣቶች ህንጸት ማዕከል ተካሄደ።
ሥልጠናው “በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ሰብዓዊነትን የማስጠበቅ ኃላፊነት” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን ብፁዓን ጳጳሳትን፣ በጠቅላይ ጽ/ቤት የሐዋርያዊ ክፍል ኃላፊ፣ ሠራተኞችን እና የማህበራዊ ተግባቦት ክፍል ሠራተኞችን፣ እና ከአስራ አንድ ሰበካዎች የተወከሉ የሚዲያ ባለሙያዎችን አሳትፏል።
በሥልጠናው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ የመጀመሪያው ሐዋሪያዊ መልዕክት (Encyclical) የሆነው “ማኚፊካ ሁማኒታስ”፤ ሥነምግባር የተሞላበት የዲጂታል ተግባቦት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ እንዲሁም ተግባራዊ የመገናኛ ብዙኃን ክህሎቶች በተለያዩ አሰልጣኞች ተሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ልሣኑክርስቶስ የባህርዳር ደሴ ሀገረስብከት ጳጳስ እና በጳጳሳት ጉባኤ የማህበራዊ ተግባቦት እና መገናኛ ብዙኃን ወኪል ጳጳስ ስልጠናውን በጸሎት በመክፈት ሐዋርያዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የመጡትን ሰልጣኞችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት የብዙሃን መገናኛ አገልጋዮች የወንጌል ስብከት ተባባሪዎች መሆናቸውን በመገንዘብ የክርስቶስን ፍቅር፣ ርኅራኄና እውነት በአገልግሎታቸው ሊገለጽ ይገባል ብለዋል።
የሰውን ክብርና ሰብአዊነት ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር በማጣጣም መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ብፁዕነታቸው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለሰው ልጅ አገልጋይ እንጂ ሰውን የሚተካ እንዳልሆነ በመረዳት ቴክኖሎጂን ለሰው ልጅ ጥቅምና ለስብከተ ወንጌል ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በሥልጠናው የተገኙትን የሀገረስብከት ጽ/ቤት የማህበራዊ ተግባቦት ተወካዮችንም የተደራጀ አገልግሎትን በማጠናከር የተማሩትን ዕውቀትና ልምድ ወደየአካባቢያቸው ወስደው በተግባር ማዋል እንዳለባቸው አስታውሰዋል።
“የእኛ ጥሪ መረጃን ማስተላለፍ ብቻ አይደለም፤ እውነትን ማስተላለፍ፣ ተስፋን ማነጽና ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማቅረብ ነው።” በማለት የሚዲያ ባለሙያዎች የብዙሃን መገናኛ የአንድነት፣ የሰላምና የስብከተ ወንጌል ድልድይ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በቆየው ሥልጠና “ሥኬታማ ተግባቦት በቤተክርስቲያን” በሚል ርዕስ በክቡር አባ ዳዊት ውብሸት የኮምቦኒ ማህበር ካህን፤ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ የመጀመሪያው የሆነው ሐዋሪያዊ መልዕክት (Encyclical) “ማኚፊካ ሁማኒታስ” ሰነድ ማብራሪያ በክቡር አባ ሚካኤል ተከስተ የአዲስ አበባ ሰበካ ካህን፣ “የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምንነት እና የወደፊት አካሄድ” በወጣት ሚኪያስ እስጢፋኖስ እና “ተግባራዊ የመገናኛ ብዙኃን ክህሎት ስልጠና” በወጣት መስቀል ኃይሌ ጨምሮ በዘርፉ ዝግጅት ባላቸው ባለሙያዎች አማካይነት ተሰጥተዋል።
ተሳታፊዎች በስልጠናው በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው በየሰበካቸውን ይህን መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እና በቴክኖሎጂ እና በቤተክርስቲያን አስተምህሮዎች አማካይነት በቀጣይነት ከጠቅላይ ጽ/ቤት የማህበራዊ ተግባቦት ቢሮ ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የአገልግሎት ዘርፉ ዘመኑን ባማከለ እና ቤተክርስቲያን ባስቀመጠችው አቅጣጫ መሰረት የሚዘጋጁ መመሪያዎች እንደሚያስፈልጉ በመግለፅ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ኃላፊነት የሚሰማቸው የሚዲያ ባለሙያ መሆን እንደሚያሰፈልግ መረዳታቻውን ገልጸዋል።
በመርሃግብሩ ማጠቃለያ በመገኘት አባታዊ መልዕክታቸውን እና ቡራኬያቸውን ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ እና የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት በበኩላቸው እያደገ በመጣው የዲጂታል አለም የስብከተ ወንጌል አቅጣጫዎቻችን እና መንገዶቻችን አብረው ማደግ እንዳለባቸው አስታውሰዋል። ብፁዕነታቸው የሚዲያ ባለሙያዎች ሥነምግባር የተሞላበት ካቶሊካዊ መንገድ ለሁሉም ድምጽ መሆን እንደሚገባ በማስታወስ ለቤተክርስቲያን የሚዲያ አገልግሎት እድገት በሥልጠናው የተሳተፉትን እና የሥልጠናውን አዘጋጆች አመስግነዋል።
