ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ።

58ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት መደበኛ ጉባኤ ሞጆ በሚገኘው የኮንሶላታ አባቶች ገዳም የሱባኤ ማዕከል ከሀምሌ 1 እስከ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ጉባኤው ሐዋርያዊ መልዕክት በማስተላለፍ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል።
በጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ መርሃክርስቶስ የሀዋሳ ሀገረስብከት ጳጳስ ከቀድሞ ጳጳሳት (በጡረታ ላይ የሚገኙ) ጋር በበርካታ ብፁዓን ጳጳሳት ተሳታፊነት የተካሄደው ጉባኤ በወቅታዊ ሁኔታዎች አለመመቻቸት ምክንያት ጉባኤው ላይ መገኘት ካልቻሉት ከብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ በስተቀር የ12ቱ ሀገረስብከቶች ጳጳሳት ተገኝተዋል።
በጉባኤው አዲስ የተሾሙት የቅድስት መንበር ተወካይ ሊቀጳጳስ ብሪያን ኡዳግዌ በመገኘት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 14ኛን የአብሮነት መልዕክት ለብፁዓን ጳጳሳት አስተላልፈዋል። ሊቀጳጳስ ብሪያን ወደኢትዮጵያ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ በጋራ ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
የቤተክርስቲያንን ኃላፊነትን ለመጋራት፣ ለተግዳሮቶች አዳዲስ የመፍትሔ ሀሳብ ለመስጠትና ለዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች አዳዲስ ጳጳስት መሾማቸው ጉባኤውን ጉባኤውን የበለጠ እንደሚያጠክረው የገለጹልን የጳጳሳት ጉባኤ የተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ተወካይ እና የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ናቸው። ጉባኤው በተለያዩ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ፣ መዋቅር፣ ተቋማት፣ ስብከተ ወንጌል፣ ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን አክለው ገልጸዋል። እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያማከሉ ውሳኔዎች እና ምክሮችን ማሳለፍ ችሏል።
ቤተክርስቲያን እንደእናት ልጆቿ በሰላም ወጥተው እንዲገቡ የዘወትር ምኞቷ እና ጭንቀቷ መሆኑን የገለጹት ብፁዓን ጳጳሳት ሀገራችን ባለችበት አሁናዊ ሁኔታ ግን ከምንግዜውም በበለጠ አንድ በመሆን ድምጻችን እንዲሰማ እንሻለን ብለዋል። ለዚሁም ማሳያ ይሆን ዘንድ ሐዋርያት ተጨንቀው በር ዘግተው በነበሩበት ወቅት ክርስቶስ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” እንዳለው፤ ብፁዓን ጳጳሳትም ይሄንኑ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ገልጸዋል። በመልዕክታቸውም ሁሉም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለሰላም ሊጸልይ፣ ሊጾም እና ሊሰራ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአንድ አባት ጥላ ስር ሆና 23 ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ የተለያዩ የሊጡርጊያ አይነት ያላቸው ቤተክርስቲያናት ባለሀብት ናት። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የምስራቅ እና የላቲን ሥርዓቶች የሚተገበሩ ሲሆን ከ13ቱ ሰበካዎች ዘጠኙ በላቲን ሥርዓት ቀሪ አራቱ ደግሞ በምስራቅ ሥርዓት የሚተዳደሩ ናቸው። ብፁዓን ጳጳሳት በኢትዮጵያ ስለሚተገበሩ የሉጡርጊያ አይነቶች የተወያዩ ሲሆን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የሚጠበቁት በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጁሬቲ ጋር ስለሚኖራቸው ቆይታ ተወያይተዋል።
የቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮ የሆነው የሐዋርያዊ አገልግሎት በጠቅላይ ጽ/ቤት በተሻለ መንገድ ለማጠናከር በአዲስ መልኩ ለመስራት የታሰበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ዘርፉን የሚያሰተባብሩ ብቁ የሆኑ ካህንም በቅርቡ ለመምረጥ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸው በሲኖዶሳዊ አብሮ የመጓዝ መንፈስ ከምዕመናን ጋር ስብከተ ወንጌል መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
የቤተክርስቲያን ተቋማት የሆኑት የጤና ጣቢያዎች፣ የትምህርት ተቋማት እና የካቶሊክ ጽህፈትቤቶቻችን አስተዳደራዊ እና የአፈጻጸም ጉዳዮች ላይ በሰፊው በመመካከር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምክረ ሀሳቦች እና ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

ብፁዓን ጳጳሳት በጉባኤያቸው መደምደሚያ በሞጆ በሚገኘው የኮንሶላታ አባቶች ገዳም የሱባኤ ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃግብር አካሂደዋል። “ውዳሴ ለአንተ” (ላውዳቶ ሲ) የተሰኘው የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ የጻፉት ሐዋርያዊ ማነቃቂያ መሰረት በየአመቱ በጉባኤያቸው ማጠናቀቂያ የሚያድርጉት የችግኝ ተከላ መርሃግብር በዘንድሮ በተለየ ሁኔታ ከህፃናት፣ ከምዕመናን እና ከገዳማውያን ጋር በህብረት ተክለዋል። በመርሃግብሩ ብፁዓን ጳጳሳት በህፃናት ዝማሬ ታጅበው ምድርን መንከባከብ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በማስተማር ልዩ ቆይታ አድርገዋል። ህፃናቱም ችግኞቹን ከጳጳሳት ጋር በመትከላቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
