የኢትዮጵያ ካቶሊክ ካሪታስ ልዑካን የCOP31 ጉባኤ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ካሪታስ ልዑካን ቡድን ወደ አንታልያ፣ ቱርክ በማቅናት 31ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ተሳትፎውን በማድረግ ላይ ይገኛል። የልዑካኑ ዋና ዓላማ ከCOP31 ልምዶችና ተሞክሮዎች መማር እና ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በህዳር 2027 በአዲስ አበባ የምታስተናግደውን COP32 ለማዘጋጀት የሚያግዙ ግንዛቤዎችን ለማግኘትና ዝግጅቶችን ለማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።
ልዑካኑ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ካሪታስ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉነህ ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ካሪታስ የCOP32 አስተባባሪ ወ/ሮ ጽዮን ነጋ እና የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት (CRS) ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አባቡ ይርጋን ያካትታል።
አቶ ሙሉነህ ተስፋዬ ቡድኑ በአንታልያ ከደረሰ በኋላ ከካሪታስ አፍሪካ፣ ከአፍሪካና የማዳጋስካር የጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM)፣ ከካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ፣ ከቅድስት መንበር፣ ከተለያዩ የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ አባል ድርጅቶች፣ ከላውዳቶ ሲ ንቅናቄ ተወካዮች፣ በቱርክ ከሚገኙት የቫቲካን ተወካይ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር የቅንጅትና የትብብር ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ለCOP31 ካቶሊካውያን ተሳታፊዎች በአንታልያ በሚገኘው የቅዱስ ኒኮላስ ቤተ ጸሎት በጀኔቫ የቫቲካን ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ባልስቴሮ የመስዋዕተ ቅዳሴ ህዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም. አሳርገዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ምዕመናን ለቤተሰቦች፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለሥራ ቦታዎች የጋራ መደጋገፍ እና መተጋገዝ እንዲኖር፤ ገና በማህፀን ላይ ላሉ ሕፃናት፣ ለልጆች፣ ለአረጋውያንና ራሳቸውን መጠበቅ ለማይችሉ ወገኖች ደኅንነት እንዲጠበቅ፤ እንዲሁም ለታመሙና ለተጎዱ ሰዎች እና ደኅንነታቸውንና ጤንነታቸውን ለሚንከባከቡ ሁሉ ጸሎት አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ አንቱዋን ኢልጊት በመስዋዕተ ቅዳሴው ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ፍጥረት ጠባቂ እና አስተዳዳሪ መሆኑን በማስታወስ የ“መክሊት” ምሳሌን ጠቅሰዋል። ምድር ለመበዝበዝ የተሰጠ ሀብት ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተሰጠች ቅዱስ አደራ መሆኗን ገልጸው፣ በአየር ንብረት ቀውስ ላይ እርምጃ አለመውሰድ፣ ቸልተኝነትና ውሳኔዎችን ማዘግየት እግዚአብሔር ያስረከበንን መክሊት ከመቅበር ጋር እኩል ነው ብለዋል። በተጨማሪም የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ፍራንቼስኮስን አስተምህሮ በመጥቀስ፣ የዓለም መሪዎችና ተደራዳሪዎች ከቃላት ወደ ተግባር በመሻገር በተለይም በአካባቢ ጉዳት በእጅጉ ለሚጎዱት ድሆችና ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ሲባል ለአየር ንብረት ፍትህ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል። በቱርክ በቅርቡ የተከሰቱትን አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጦች እና ለዚህ የቤተ ክርስቲያንን ምላሽ በማስታወስ፣ እውነተኛ አመራር በአገልግሎት፣ በአንድነት እና በተግባራዊ ሥራ እንደሚገለጥ አስረድተዋል። በመጨረሻም የCOP31 ተሳታፊዎች ፍጥረትንና ትውልድን እንዲጠብቁ እና የጋራ ቤታችንን ለመንከባከብ ለተሰጣቸው መለኮታዊ ጥሪ በታማኝነት እንዲመልሱ አሳስበዋል።
በእነዚህ መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ካሪታስ ልዑካን ከCOP31 ተሞክሮዎች በመማር በኢትዮጵያ የሚካሄደው የCOP32 ጉባኤ ስኬታማ፣ አካታች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ለሚደረገው የተቀናጀ ዝግጅት አስተዋፅኦ ለማበርከት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
