የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ የሲኖዶስ ትግበራን በተመለከተ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ ህብረት የሆነው አመስያ (AMECEA) ላለፉት አራት አመታት በዝግጅት ላይ ቆይቶ እ.ኤ.አ 2024 ዓ.ም. በጥቅምት ወር የተጠናቀቀውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የትግበራ ሰነድ ሂደትን በተመለከተ የምክክር ጉባኤ ተጀመረ።
ጉባኤው ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያንን ጨምሮ የህብረቱ አባል የሆኑት 9ኙንም ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ማላዊ እና ኡጋንዳ የጳጳሳት ተወካዮችን አሳትፏል።
በኢትዮጵያ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት እና በአመስያ አስተባባሪነት በአዲስ አበባ የኮንሶላታ ማርያም አባቶች ገዳም ከመስከረም 19 እስከ 22 2018 ዓም. የሚካሄደው ጉባኤ የሲኖዶስ ሰነድን በተግባር ላይ ለማዋል ከቅድስት መንበር በወጣው አቅጣጫ ላይ መሰረት በማድረግ ብፁዓን ጳጳሳት ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በጳጳሳት ደረጃ የሚካሄደው ይህ የምክክር ጉባኤ በሲኖዶስ ሂደት ወቅት ሀገራቱ የነበራቸውን ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት፣ በሂደቱም የገጠማቸውን ተግዳሮት የሚወያዩበት እና ቀጠናዊ አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት መሆኑ ተገልጿል።
የአመስያ ጽ/ቤት የማህበራዊ ተግባቦት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ክቡር አባ አንድሪው ካውፋ የስብሰባው ዋና አላማ የሲኖዶስ ትግበራ ሂደትን መገምገም መሆኑን ገልጸው ቅድስት መንበር ባስቀመጠችው መርሃግብር መሰረት እ.ኤ.አ 2027 ድረስ በሁሉም የጳጳሳት ጉባኤዎች የሲኖዶስ ሰነድን በተግባር ላይ ማዋል እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል። በመቀጠልም እ.ኤ.አ 2028 በቫቲካን ለሚካሂደው ጉባኤ በሀገራት፣ በቀጠናቸው እና በአህጉር ደረጃ የተሰሩ ስራዎች እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በበኩላቸው የሲኖዱን ሰነድ በተግባር ላይ ለማዋል ሁሉም የቤተክርስቲያን አካላት በቅድሚያ ሰነዱን በጥልቀት ማንበብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ይህንንም በማድረግ የቤተክርስቲያን መሰረት በሆነው እውነተኛ ቤተሰብ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የቀጠናው ከፍተኛ ቁጥር የያዘውን ወጣቶችን በሲኖዶሳዊ አብሮነት መንፈስ መጠበቅ እና መንክባከብ እንደሚያስፈልግ እና የሲኖዱን ሰነድ በተግባር ላይ ለማዋል ሁሉም ከቤተክርስቲያን ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
