የብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ እና የብፁዕ አቡነ ጸጋዬ 50ኛ ዓመት የክህነት አገልግሎት በመስዋዕተ ቅዳሴ ተከበረ

ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ እና የብፁዕ አቡነ ጸጋዬ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዪ የክህነት አገልግሎት በልደተ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል በመስዋዕተ ቅዳሴ ተከበረ።

ብፁዕ ካርዲናል መስዋዕተ ቅዳሴውን ከብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ ጋር ያሳረጉ ሲሆን በመስዋዕተ ቅዳሴው ብፁዕ ሊቀጳጳስ ብሪያን በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ ብፁዕ አቡነ ስዪም የሆሳዕና ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ደጀኔ የሶዶ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ምዕመናን እና ግብዣ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

የዕለቱን ቃለ ምዕዳን ያስተለፉት ክቡር አባ ግሩም ተስፋዬ በካቶሊካውያን ዘንድ በዛሬው ዕለት በሚከበረው የቅዱስ ጳውሎስ እና የቅዱስ ጴጥሮስ በዓል እኛም የታላላቅ ብፁዓን አባቶቻችንን የቅድስና መንገድ የምንመስክርበት ቀን ሆኖልናል ብለዋል። በወንጌሉ “ሁሌም ለክርስቶስ ሰው ይበልጣል” ያሉት ክቡር አባ ግሩም ብፁዓን ጳጳሳቱም የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ክብር በማስቀደም ከ50 ዓመታት በላይ የሆነ የአገልግሎት ምስክር ሆነዋል ብለዋል።

በመንፈሳዊ ህይወታቸው የቅድስና ምስክርነት መስጠት የቻሉት ብፁዓን ጳጳሳቱ የካቶሊካዊት ቤትክርስቲያን ቅዱሳን ከሆኑት በጥቂቱ ቅድስት እማሆይ ተሬዛን (Mother Teresa)፣  ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛን፣ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን እንዲሁም ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በሕይወት በማግኘት ቡራኬ መቀበል ችለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ የመልካም ምኞት መልዕክት በቅድስት መንበር ተወካይ ብፁዕ ሊቀጳጳስ ብሪያን አማካይነት የቀረበ ሲሆን ቅዱስነታቸው ብፁዓን ጳጳሳቱ ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለነበራቸው አስተዋፅዖ እና የአገልግሎት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

ለብዙዎች አብነት እና የአገልግሎት ጽናት ተምሳሌት የሆኑት ብፁዓን ጳጳሳቱ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እድገት ውስጥ ከፍተኛ አሻራ እንዳላቸው ተገልጿል። በተለይም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ያበረከቱት አስተዋፅዖ የላቀ ነው። ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በጠቅላይ ጽ/ቤት ፕሬዝደንት ሆነው ከ26 አመት በላይ ያገለገሉ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ደግሞ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አሁናዊ መዋቅሩን በማደራጅት ለ 9 ዓመት በጠቅላይ ጸኃፊነት አገልግለዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው ማጠቃለያም ብፁዕ አቡነ ደጀኔ እና ብፁዕ አቡነ ስዪም ሰበካቸውን በመወከል፣ ክቡር አባ ከተማ አስፋው ብፁዓን ጳጳሳትን እና ጠቅላይ ጽ/ቤቱን በመወከል፣ ክቡር አባ ታመነ አሳሮ ገዳማውያን እና ገዳማውያትን በመወከል፣ ክቡር አባ መምህሩ የማህበረ ልዑካን (ላዛሪስት) ገዳምን በመወከል፣ ክቡር አባ ፍስሃ የኢትዮጵያ ካህናት ማህበርን በመወከል፣ ክቡር አባ ታምራት የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ካህናት እና ቆሞሳት ማህበርን በመወከል፣ እንዲሁም ክቡር አቶ ሚልክያስ ምዕመናንን በመወከል ስለብፁዓን ጳጳሳቱ አገልግሎት ምስክርነት እና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱም በበኩላቸው በአገልግሎት ዘመናቸው ላገዟቸው እና በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ለምስጋና የመጡትን ሁሉ አመስግነው መስዋዕተ ቅዳሴው ተጠናቅቋል።

አቡነ ጸጋዬ “ለአገልግሎት እድል የሰጠችኝን ቤተክርስቲያንን አመሰግናለሁ” በአገልግሎት ዘመናቸው ላገዟቸው ሁሉ አመስግነዋል ለጉዞዬ ፋና የሆኑልኝን ወጣት እና ተተኪ ካህናትን እና ብፁዓን ጳጳሳት የልዩ ደስታዬ ምክንያት ናችሁ በማለት አመስግነዋል ቤተሰቦችን ምዕመናንን ሁሉ ለዛሬዎቹ ወጣቶች የክርስቶስን ፍቅር ላወርሳችሁ እወዳለሁ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ፈፃሚ ናችሁና ክርስቶስን ብቻ አስቀድሙ።


Leave a Reply

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300