ላለፉት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት የሲኖድ ትግበራ የምክክር ጉባኤ ተጠናቀቀ።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲኖድ የትግበራ ሂደትን በተመለከተ በአዲስ አበባ የኮንሶላታ ማርያም አባቶች ገዳም ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረግ የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ ህብረት የሆነው አመስያ (AMECEA) አዘጋጅነት በኢትዮጵያ የተካሄደው ይህ ጉባኤ የቀጠናው አባል ሀገራት ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የሲኖድ ተወካይ ጳጳሳትን እና የጠቅላይ ጽ/ቤት ጠቅላይ ጸኃፊን አሳትፏል።
በጉባኤው የሲኖድ ሰነድን በተግባር ላይ ለማዋል ከቅድስት መንበር በወጣው አቅጣጫ ላይ መሰረት በማድረግ ብፁዓን ጳጳሳት የተወያዩ ሲሆን ይህም ሰነድ እና የቤተክርስቲያን መመሪያ በቀጣይ ተፈጻሚ እንዲሆን አስቻይ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

በተጨማሪም ሀገራቱ በሂደቱ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በመድረኩ ያጋሩ ሲሆን ከዚያም በመነሳት የልምድ ልውውጥ ማድረግ መቻሉን በተሳታፊዎች ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ይህን ሰነድ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እና ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን የአመስያ ጽ/ቤት በበኩሉ በሲኖድ ሰነድ አቅጣጫ መሰረት በቀጣይ የሚኖሩ በርካታ የውይይት፣ የግምገማ እና የአፈጻጸም ክትትል መደረኮችን እንደሚያዘጋጅ ገልጿል።
ጉባኤውን የመሩት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ ይህ ጉባኤ የሲኖዱን አተገባበር በቀጠናው የተቀናጀ ለማድረግ የተካሄደ ሲሆን በስብሰባው የተሳተፉት ብፁዓን ጳጳሳት ከዚህ ቀደም አመስያን እና ሀገራቸውን በመወከል በቅድስት መንበር የተገኙ ተወካይ ጳጳሳትን መሆናቸውን ገልጸዋል። በስብስባው ማጠቃለያም የቅድስት መንበርን መመሪያ መሰረት በማድረግ የአመስያ የሲኖድ ትግበራ አጋዥ ሰነድ እንደሚወጣም አሳውቀዋል። ጉባኤው አዲስ አበባ እንዲሆን የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቀበል ለጋበዙት ለብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ፣ የአመስያ ጽ/ቤት፣ በአዲስ አበባ ለነበራቸው መልካም ቆይታ ትብብር ላደረጉት ለጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር እና ሠራተኞች፣ ለኮንሶላታ አባቶች እና ለሶቨሬን ኦርደር ኦፍ ማልታ ኤምባሲ (Sovereign Order of Malta ) ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በጉባኤው በማጠቃለያ መርሃግብር ብፁዕ አቡነ ብሪያን ኡዳግዌ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ተወካይ በመገኘት አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በመዝጊያ መርሃግብር ብፁዓን ጳጳሳት የአድዋ ሙዚየም እና የኢዮቤልዩ ቤተመንግስት ጉብኝት አድርገዋል።

