ላለፉት 4 ቀናት ቀናት በመካሄድ ላይ የቆየው የሲኖዶስ“የመጨረሻው ሰነድ” በአማርኛ ላይ ያተኮረ አውደጥናት ተጠናቀቀ

ከህዳር 2 አስከ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሞጆ የኮንሰላታ አባቶች ገዳም ሲካሄድ የቆየው አውደጥናት የትግበራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ።
ጉባኤው የሁሉም ሀገረስብከቶች ተወካዮችን በማሳተፍ፣ ከተጠበቀበት ዓላማ እና የወደፊት የትግበራ አቅጣጫዎችን ከማስቀመጥ አንጻር ከግብ መድረስ እንደተቻለ በተጨማሪም በሲኖዶስ አብሮ የመጓዝ እና የማገልገል መንፈስን ማደስ መቻሉን የሐዋርያዊ ሥራዎች ክፍል እና የአውደጥናቱ አስተባባሪ ክቡር አባ አብርሃም ገብረማሪያም ገልጸዋል።
በሲኖዶስ ሂደት ሁሉም የመፍትሄ አካል በመሆን አብሮ መጓዝ የሚችልበት መሆኑን ማረጋገጥ የተቻለበት ይህ አውደጥናት ተሳታፊዎች ይህንን በተግባር ላይ ለማዋል ኃላፊነት ወስደዋል።
በማጠቃለያም ይህን የቤተክርስቲያን ሰነድ ወደሁሉም የቤተክርስቲያን አካላት ለማድረስ በጽ/ቤቶች አማካይነት ጥረት የሚደረግ ሲሆን በተለይም ግን ከምዕመናን ጋር በመተባበር ለሁሉም ተደራሽ እንዲሚሆን ተገልጿል።
የጉባኤው አንዱ አካል የሆነው የሐዋሪያዊ እና የልማት ሥራዎች የጋራ ጥምረት እና አብሮ የመጓዝ ሂደት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም በትምህርት ቤቶች ዘርፍ ያሉ የመተዳደሪያ ድንብ ለውጦች ላይ በመወያየት አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል።

