“ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን በኅብረት፣ ተሳትፎ፣ ተልእኮ” የሲኖዶስ የመጨረሻው ሰነድ በአማርኛ ለብፁዓን ጳጳሳት እና ለቤተክርስቲያን ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉባኤ ተካሄደ።

ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሐዋርያዊ ስራዎች ጽ/ቤት አስተባበባሪነት የተዘጋጀውን ሰነድ ብፁዓን ጳጳሳት በተገኙበት ተባርኳል። ጉባኤው በእምድብር ሀገረስብከት ከብፁዓን ጳጳሳት ጋር ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ደናግል፣ የምዕመናን ተወካዮች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የቤተክርስቲያን ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል። የመጨረሻው የሲኖዶስ የመተግበሪያ ሰነድ በክቡር አባ ምስራቅ ጥዩ በአማርኛ ትርጉም የተዘጋጀ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የሰነዱን ግብዓት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
የሲኖዶስ የመጨረሻው ሰነድ የቤተክርስቲናችን መንፈሳዊ መታደስ በኅብረት፣ ተሳትፎ፣ ተልእኮ እንዲሆን ጥሪ የሚያቀርብ ሲሆን ሲኖዶሳዊነት የቤተክርስቲያን ህይወት እና ተልዕኮ መሆኑን ይገልጻል።
“ሕዝበ እግዚአብሔር በሙሉ የስብከተ ወንጌል ልዑክ (መልዕክተኛ) ነው። ሁላችንም ተልዕኮ የተቀበልን ደቀ መዛሙርት ነን፤ በመሆኑም የተጠመቀ ሁሉ የስብከተ ወንጌል ተዋናይ እንዲሆን ተጠርቷል።” ከሰነዱ ቁጥር 53 የተወሰደ
ለሲኖዶስ የትግበራ ሂደት ቅድስት መንበር እ.ኤ.አ ከ2025 እስከ 2028 በዝርዝር መርሃግብር የተቀመጠ ሲሆን በያዝነው ዓመት በመጀመሪያ ደረጃ ሰነዱን የማስተዋወቅ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮች የሚደረጉ ሲሆን በሀገራችን በአማርኛ የተተረጎመ ቢሆንም በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም እና ለመላው ካቶሊካውያን ለማድረስ የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የመጨረሻው ሰነድ በአምስት ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበ ሲሆን በክፍል አንድ የሲኖዶሳዊነት ዋና ማዕከል በመንፈስ ቅዱስ የተጠራ የመለወጥ ጥሪ፤ በክፍል ሁለት ሁሉም በአንድነት በጀልባው ላይ የግንኙነት የለውጥ ሒደት፤ በክፍል ሦስት ለማስገር መረቡን ጣል የሂደቶች መለወጥ፤ በክፍል አራት የተትረፈረፈ ምርት የመተሳሰሪያ (የመገጣጠሚያ) ሰንሰለቶች መለወጥ፤ እንዲሁም በመጨረሻው ምዕራፍ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ ሕዝብን ለሐዋርያዊ አገልግሎት ደቀ መዛሙርት ማድረግ እና ለሁሉም የተዘጋጀ ግብዣን በመደምደሚያው ላይ በማድርግ በ155 ቁጥሮች ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት አብሮ መጓዝ በቃል ብቻ ሳይሆን ነባራዊ የሀገራችንን ሁኔታዎች በጥልቅ በመመልከት እና በመረዳት መደማመጥ የሰፈነበት ሊሆን ይገባል ብለዋል። ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው በ1960 ዓ.ም. በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ ብፁዓን ጳጳሳት መልዕክት ያስታወሱ ሲሆን ከብፁዓን አባቶቻችን የተረከብነውን እምነት እና ሃይማኖት በኃላፊነት በመውሰድ ከቀድሞ አባቶቻችን እንዲሁም ከዛሬዎቹ ወጣቶች እና ህፃናት ጋር አብረን ልንጓዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ጉባኤው በመቀጠል ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎች እና ሀሳቦች ላይ የተወያየ ሲሆን በቀጣይ ሰነዱን በተግባር ላይ ለማዋል የሚረዱ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ተችሏል።
የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ክቡር አባ ከተማ አስፋው ለሰነዱ ዝግጅት እና ተጠናቅቆ እዚህ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን ክቡር አባ ምስራቅ ጥዩን አመስግነዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሰነዱን በተመለከተ ተጨማሪ መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉባኤዎችን እንደሚያመቻች ገልጸዋል።
