ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቶሊክ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምን ጎብኝተው ለጤናና ማህበራዊ ልማት የመንግስት ቀጣይ ድጋፍ አረጋገጡ

ታህሳስ 16 ቀን 2018 ዓ.ም — የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም (ኢኩስታ) ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተሳትፈዋል።

ጉብኝቱ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኩል በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  መሪነት ከብፁዓን ጳጳሳት፣ ከክቡራን ካህናትና ከገዳማውያን ጋር ተካሂዶ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ወንድም ካሱ ፋንታዬ የተቋሙን የትምህርት መስኮችና የሚሰጡ አገልግሎቶች ለእንግዶቹ አብራርተዋል።

በውይይቱ የቤተክርስቲያኗ ለረዥም ጊዜ ያልተፈታ የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ፣ ለማህበረሰቡ የሚሰጡ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን በተሻለ አቅም ለማሳደግ ያሉ ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም የጤና አገልግሎቶችን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስፈልገው የመንግስት ድጋፍ ተነስተው ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጤናና በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ያላት አስተዋፅኦ የብዙ ዜጎችን ሕይወት መቀየሩን ጠቅሰው፣ በተቋሙ የተመለከቱት ተግባራት በሀገሪቱ የሕክምና መመርመርና ማከም አቅም ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

“ተቋሙ በቶሎ ሁለንተናዊ አገልግሎቱን እንዲጀምር በመንግስት በኩል የሚያስፈልጉ ድጋፎች ሁሉ ይደረጋሉ” ሲሉም አረጋግጠዋል።

ቤተክርስቲያኗ ዩኒቨርስቲውን ለመገንባት የፌደራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናዋን ገልጻ ለወደፊት የሚታሰቡ የግንባታ ፕሮጀክቶችም የመንግስት ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም (ኢኩስታ) በአሁኑ ወቅት 416 ተማሪዎችን በህክምና ሳይንስ፣ በላቦራቶሪ ቴክኒሺያን፣ በማህበራዊ አገልግሎት፣ በማስተማር ላይ ስትገኝ በቀጣይም በኮምፒውተር ሳይንስ እና በሒሳብ እና ፋይናንስ ዘርፍ ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት ገልጸዋል።

Saint of the day

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300