ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ አባ ኃይለማሪያም መድህንን የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ “ኮ – አጁተር” እንዲሆኑ ሰየሙ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ ክቡር አባ ኃይለማሪያም መድህንን አዲሱ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ “ኮ-አጁተር” ብለው መሰየማቸውን የቅድስት መንበር መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. አውጇል።
ክቡር አባ ኃይለማሪያም የቅዱስ ዶን ቦስኮ ገዳም አባል ሲሆን እ.ኤ.አ በ1973 በሰሜን ኢትዮጵያ አሊቴና ከአባታቸው መድህን ተስፋይ እና እናታቸው አምለሱ ወልደስላሴ ተወለዱ። የቅዱስ ዶን ቦስኮ ሳለዝያውያን ገዳም አባል ለመሆን በአዲስ አበባ ጎተራ በሚገኘው የቅዱስ ዶን ቦስኮ ገዳም የተመክሮ አመትን በማድረግ በአ.አ. 1995 የመጀመሪያ መሓላ አድርገዋል እንዲሁም በአ.አ. 2001 የመጨረሻ መሓላን አድርገዋል፡፡ የክህነት ትምህርታቸው በዓዲግራት በሚገኘው የሃገረ-ስብከቱ ሰሚናሪ በመከታተል በእ.ኤ.አ ግንቦት 4 ቀን 2003 በአዲግራት ሀገረስብከት ማዕረገ ክህነት ተቀብለዋል።
ክቡር አባ ኃሀይለማሪያም የክህነት ማዕረግ ከተቀበሉበት ግዜ አንስቶ በበርካታ ሐዋርያዊ እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከእነዚህም በጥቂቱ በአዲግራት ሀገረስብከት በአድዋ የቅዱስ ዮሐንስ ቦስኮ ሳዝያውያን ገዳም እንደ ቆሞስና የተማሪዎች አለቃ፣ እንዲሁም የቤቱ ምክትል አለቃ (እንደራሴ)፤ በኬንያ (ዶን ቦስኮ ኡቱመ) የትምህርተ መለኮት መመህር፣ በአዲስ አበባ ዶን ቦስኮ መካኒሳ የገዳም አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሳሊዥያን ገዳም አለቃ እና የኢትዮጵያ ገዳማት የበላይ አለቆች ማህበር ፕሬዝድንት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ክቡር አባ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአስር አመት ዕቅድ ዝግጅት ሂደት ውስጥም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ አባት ናቸው።
ክቡር አባ ኃይለማሪያም ሮም ከሚገኘው የሳሌዢያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሰቲ፡ በነገረ-መለኮት፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን በመቀጠልም በተመሳሳይ ዪኒቨርስቲ በነገረ መለኮት የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ደስታውን እየገለጸ ለክቡር አባ ኃይለማሪያም መድህን የተባረከ የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኛል።
