የሲስተር ካትሪን ጋይኖር አጭር የህይወት ታሪክ

የፍቅር ሥራ ልጆች ገዳም አባል የሆኑት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ የማህበራዊ ተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል መስራች በመሆን ያገለገሉት ክብርት ሲስተር ካትሪን ጋይኖር በ1927 በዱብሊን አየርላንድ ተወለዱ። 

የቅዱስ ቬንሰንትን “ድሆችን የሚወዱ ሞትን አይፈሩም” የሚለውን ቃል በሙላት መኖራቸው የሚመሰከርላቸው ሲስተር ካትሪን በ1951ዓ.ም. የፍቅር ሥራ ልጆች ገዳም አባል በመሆን ህይወታቸው በርህራሄ በተሞላ አገልግሎት የኖሩ ሲሆን ድጋፍ እና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ በደስታ እና በማያቋርጥ ቁርጠኝነት እድሜያቸውን ሰጥተው ኖረዋል።  ደግነታቸው እና ልግስናቸው በበርካቶች ዘንድ ህይወትን የቀየረ ሲሆን በተለይም ለድሆች እና ለተገለሉ ሰዎች የመኖርን ተስፋን መልሰዋል።  

ሲስተር ካትሪን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት እ.ኤ.አ በ1969 ሲሆን አገልግሎታቸውን በቅድስት ማርያም ገዳም ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ማርያም የሴቶች ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በመሆን ለአስር አመታት አገልግለዋል። በመቀጠልም ወደ ብሪታኒያ ለአጭር ቆይታ የተጓዙ ሲሆን በ1981 ወደኢትዮጵያ በመመለስ እስከ 2005 አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል። ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች በነበራቸውም ልዩ ርህራሄ እና በጥበብ የተሞላ አገልግሎት ብዙዎችን በራሳቸው እንዲተማመኑ እና አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ አስችለዋል። በሲስተር ካትሪን ያላሰለሰ ጥረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ልጃገረዶች የትምህርት እድል አግኝተዋል፣ እንዲሁም በርካታ ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ግለሰቦች እንክብካቤ፣ ፍቅር እና ተስፋን አግኝተዋል።

ሲስተር ካትሪን ለማህበረሰቡ ካበረከቱት ሰብዓዊ አገልግሎት ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የማህበራዊ ተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል በመመስረት እና ተልዕኮውን ለማስቀጠል ሰራተኞችን በማሰልጠን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሰፊ ማህበረሰብ የስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ በዘርፉ ዘላቂ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በክፍሉም ከነበራቸው አስተዋጽዖ የፍቅርና ሰላም ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ሀገረስብከት በመረከብ በጳጳሳት ጉባኤ ደረጃ የመጀመሪያውን ወርሃዊ ጋዜጣ ማስጀመራቸው፣ የሬድዮ እና የድምጽ መቅጃ ስቱዲዮ ማስገንባታቸው፣ የካቶሊክ የስልክ እና አድራሻ መዝገብ ማስጀመራቸው፣ እና የቤተክርስቲያኗን አገልግሎቶች በተንቀሳቃሽ ምስል እንዲቀመጡ ለማስቻል መሳሪያዎችን በማሟላት እና ባለሙያዎችን በስልጠናዎች በማብቃት የሰጡት አገልግሎት ከብዙዎቹ በጥቂቱ ይገለጻሉ። ጡረታ እስከወጡበት ግዜ ድረስ በዚህ ቢሮ ውስጥ ያለመታከት በኃላፊነት አገልግለዋል።

በ2005 በጤና ምክንያት ወደ አየርላንድ ከተመለሱ በኋላም ቢሆን፣ ሲስተር ካትሪን ከኢትዮጵያ እና ከሕዝቦቻቸው ጋር ጥልቅ ግንኙነት ነበራቸው።

ሲስተር ካትሪን በእምነታቸው፣ በትህትናቸው እና በደስታ የተሞላ የአገልግሎት ህይወታቸው ብዙዎችን አነሳስተው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው አርፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ እግዚአብሔር አምላክ ለሲስተር ካትሪን ዘላለማዊ ዕረፍት እንዲሰጥልን እንጸልያለን።


Leave a Reply

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300