የብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ አጭር የሕይወት ታሪክ

“ሀምሳ ዓመታት የክህነት አገልግሎት፤ ሰብዓዊነት ከመሪነት በላይ”
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ከአባታቸው ከአቶ ሱራፌል አደፍርስ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሥነድንግል ቢራቱ ሐምሌ 7 ቀን 1940 ዓ.ም. በቀድሞው ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ በምዕራብ ሐረር ኦሮሚያ ዞን በአንጫር ወረዳ በጨለለቃ ከተማ ተወለዱ። ለቤተሰቦቻቸው አምስተኛ ልጅ የሆኑት ብፁዕነታቸው በላፍቶ ጎባ ቅዱስ ገብርኤል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ጥምቀት ተቀብለው ብርሃነኢየሱስ ተብለው የክርስትና ስም ተሰጣቸው። ልጅነታቸውን ከብቶችን በመጠበቅ፣ ከወንዝ ውኃ በመቅዳት ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ አድገው ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቅዱስ ሚካኤል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቄስ ትምህርት ቤት ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአቃቂ በሰቃ የመንግሥት ትምህርት ቤት በመግባት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ጀመሩ። በመቀጠልም ወደ ድሬዳዋ በመመለስ በቅዱስ አውጉስጢኖስ አዳሪ ትምህርት ቤት በመግባት በብስራተ ገብርኤል 1ኛ እና 2ኛ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመከታተል ላይ እንዳሉ የመንፈሳዊ ትምህርትም በመማር ምሥጢረ ቁርባንና ምሥጢረ ሜሮን በድሬዳዋ ቅዱስ አውጎስጢኖስ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ዑርባኖስ እጅ ተቀብለዋል።
የመንፈሳዊ ሕይወት ዝንባሌ በይበልጥ ያደረባቸው ገና በ5ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ የላዛሪስት ገዳም ማኅበር አባል የነበሩትና የቀድሞ የነቀምቴ ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፍቅረማርያም ገመቹ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ መጥተው ስለክህነት ጥሪና መንፈሳዊ አገልግሎትን በተመለከተ ባስተላለፉት ትምህርት ገለጻ በመማረካቸው ነበር። በክረምት ለዕረፍት ወደቤተሰቦቻቸው በሄዱበት ጊዜ ለወላጅ አባታቸው ስለ ክህነት ጥሪ በመንገርና ሀሳባቸውን በመግልጽ ምክር ሲጠይቁ አባታቸው የነገሯቸውን ዘወትር ያስታውሳሉ። ክህነት ከባድ ኃላፊነት መሆኑና ካህን ለመሆን ካሰብህ እግዚአብሔርንና ሰውን ማሳዘን እንደሌለባቸው፣ ክህነትን ከሚያበላሹ ነገሮች መራቅ እንዳለባቸው ከነገሯቸውና ከመከሯቸው በኋላ “ከወደድከውና ካመንክበት ዝንባሌህን መፈጸም ትችላለህ” በማለት ፈቃዳቸውን እንደገለጹላቸው፤ በይበልጥ የተሻለ ምክር እንዲያገኙም በአካባቢው ወደነበሩት ካህን መላካቸውን ያስታውሳሉ። በጊዜው በላፍቶ ጎባ ቅዱስ ገብርኤል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቆሞስ ወደነበሩት ወደ ክቡር አባ ሮናልድ ላቤ (የፈረንሳይ ካፑቺን) በመሄድ የክህነት ጥሪ እንደተሰማቸው ካህን መሆን እንደሚፈልጉ በመግልጽ ምክር ሲጠይቁ ቆሞሱም የወጣቱን የደምረው ሱራፌልን ሐሳብ በማበረታታትና በመደገፍ ጊዜውን ጠብቆ በአዲስ አበባ ላዛሪስት ንዑስ ዘርዓ ክህነት እንዲገቡ የድጋፍ ደብዳቤ ጻፉላቸው።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ላዛሪስት ንዑስ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ተከታትለው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት በታላቅ ማዕረግ አጠናቅቀዋል። ወጣቱ ደምረው ሱራፌል በወቅቱ በነበራቸው የክህነት ጥሪ ሕይወታቸውን ወደ መንፈሳዊነት በመምራት የፍልስፍና ትምህርት በቅዱስ ካሌብ ዓብይ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት እና በልዩ ምዝገባ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (በአዲስ አበባ) ዪኒቨርስቲ የአንደኛውን ክፍለ ትምህርት የሆነውን የፍልስፍና ትምህርት አጠናቅቀዋል። በዓላማቸው ጸንተውና ትጉህ ሆነው ያገኟቸው የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት አለቆች ወደ እንግሊዝ ሀገር ልከዋቸው በለንደን ሚሽነሪ ኢንስቲትዩት እና በለንደን ዩኒቨርስቲ ኪንግስ ኮሌጅ የነገረ መለኮት ትምህርት ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ወደ አገራቸው በመመለስ በ1967 ዓ.ም. ለተመክሮ ነቀምት ሀገረስብከት በሚገኘው ኮንቺ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተመድበው የኮንቺ መድኃኔዓለም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዪ በኋላ የድቁና ማዕረግ በዚሁ ቤተክርስቲያን በ1968 ዓ.ም. ተቀብለዋል። ምሥጢረ ክህነታቸውን ደግሞ በብፁዕ አቡነ ኤቴልዶርፍ ሰኔ 27 ቀን 1968 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ላዛሪስት ገዳም በምትገኘው ጽዮን ማርያም በቀድሞ መጠሪያዋ /በፍልሰታ ለማሪያም/ ቤተክርስቲያን የላዛሪስት ገዳም ሙሉ አባል ሆነው ማዕረገ ክህነት ተቀብለዋል። ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በመቀጠል በ1969 ዓ.ም. በደምቢዶሎ ወለጋ እና ከ1970 – 1971 ዓ.ም. በጅማ ቦንጋ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ቆሞስ በመሆን አገልግለዋል። በዚህም ወቅት በጅማና በቦንጋ አካባቢ በተካሄደው የሃይማኖት ስደት ምክንያት በክህነት አገልግሎት እንዳይቀጥሉ በጅማ ወህኒ ቤት ለሰባት ወር የታሰሩ ሲሆን እንደተፈቱም ከጅማ አገልግሎታቸውን አቋርጠው ለመውጣት ተገድገዋል።
በተከታዮቹ ዓመታት ማለትም ከ1972 – 1975 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደሮም ተልከው በግሪጎሪያን ዪኒቨርስቲ በማህበራዊ ሳይንስ ፋክልቲ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪ ተቀብለዋል።
ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከ1975 – 1983 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ላዛሪስት ገዳም በዘርዓ ክህነት ቤተ ተመክሮ በዳይሬክተርነት፣ በገዳም አስተዳዳሪነት፣ የማርያም ጽዮን ቤተክርስቲያን ቆሞስ በመሆን እያገለገሉ ሳሉ በተጨማሪ በቅዱስ ፍራንቼስኮስ የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ተቋም ሲያስተምሩ ቆይተዋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተሰብ ዕድገት ማደራጃን መመሥረት ችለዋል። በ1984 ዓ.ም. የብፁዕ አቡነ ፍቅረማርያም እንደራሴ በመሆን ወደ ጅማ ተመልሰው እያገለገሉ እያሉ ጷግሜ 3 ቀን 1986 ዓ.ም. የጅማ ቦንጋ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው እንዲያገለግሉ በወቅቱ በነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተሾሙ።

ይህንን አገልግሎታቸውን በትጋትና የምእመናንን ፍላጎት ለማሟላት በመጣር ሲያገልግሉ ቆይተው ኅዳር 12 ቀን 1990 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ አሁንም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተሾሙ። ሲመተ ጵጵስናቸውም በአዲስ አበባ ልደተ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ጥር 17 ቀን 1990 ዓ.ም. በብፁዕ አባታችን ካርዲናል ጳውሎስ ጻድዋ እጅ በምስራቅ አብያተ ክርስቲያን ሕገ ቀኖና ደንብና ሥርዓት “በጥበቃሽ ሥር” በሚል የጵጵስና አገልግሎት መሪ ቃል ተከናውኗል።
በ1991 ዓ.ም. ብፁዕ ካርዲናል ጳውሎስን በመተካት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሊቀ ጳጳስነት ኃላፊነት ተረከቡ። ከዚህም በተጨማሪ ከብዙ በጥቂቱ በዋናነት ከዚህ በታች በተጠቀሱ ክፍሎች አገልግለዋል።
- ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት
- ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ በቅድስት መንበር ቫቲካን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት አማካሪ
- ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ካቶሊክ ዪኒቨርስቲ መስራች እና ቻንስለር
- ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ በአባልነት የምትገኝበትን የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በሰላምና በወንድማማችነት ዙሪያ የበላይ ጠባቂ
- በ2007 ዓ.ም. የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (AMECEA) በሊቀ መንበርነት ለ4 ዓመት እንዲመሩ ተመርጠው አገልግለዋል
- ታኅሣሥ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለካርዲናልነት ማዕረግ በመታጨት በየካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በእኩለ ሌሊት በተደረገው መሥዋዕተ ቅዳሴ ክብረ በዓል የካርዲናልነት ማዕረግን ተቀብለዋል።
- በየካቲት 2011 ዓ.ም. የእርቀሰላም ኮሚሽን ፕሬዝደንት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፓርላማ የተመረጡ ሲሆን በሀገሪቱ የሰላም እንዲሰፍን ከኃይማኖት አባቶች እና ከበርካታ አካላት ጋር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በማስተባበር አገልግለዋል። በ2017 ዓ.ም. የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ በሕይወት በመለየታቸው ቀጣዩን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ለመምረጥ በቫቲካን ቅድስት መንበር በመገኘት በካርዲናሎች ጉባኤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ካርዲናል ሆነው በምርጫው ላይ በመሳተፍ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛን መርጠዋል።
ብፁዕነታቸው የሐዋርያዊ እና የአስተዳደራዊ አገልግሎታቸውን በመቀጠል እያደገች ባለችው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እጅግ በርካታ እና ዘርፈ ብዙ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ብፁዕነታቸው የእምድብር፣ የባሕርዳር ደሴ፣ እና የጋምቤላ ሀገረስብከቶችን እንዲሁም የባሌ ሮቤ ሐዋርያዊ አስተዳደርን እንዲመሠረቱ ከፍተኛውን ኃላፊነት በመወጣት እንዲቋቋሙ አድርገዋል። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የአሥራ ሦስትቱንም የኢትዮጵያ ሀገረስብከቶች የሚመሩትን ብፁዓን ጳጳሳት ቅብዓተ ጵጵስና የመሩ ሲሆን በጡረታ እረፍት ላይ ያሉ ጳጳሳትን ጨምሮ ከ21 በላይ ጳጳሳትን ቀብተዋል። ከ45 በላይ ካህናትን እና እጅግ በርካታ ደናግል፣ እንዲሁም በተለያየ ጥሪ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ ምዕመናንን ማብቃት ችለዋል።
ብፁዕነታቸው ቤተክርስቲያንን በመወከል በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጎ ፍቃድ ካላቸው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ለሰላም እና ለፍትሕ በመቆም ለተጎዱ እና ለንጹሐን ድምጽ ሆነዋል።
ብፁዕነታቸው በጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ ጽ/ቤት ፕሬዝደንትነት ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገለሉ ሲሆን ከአምስት ጠቅላይ ጸኃፊዎች ጋር እና ከሀገሪቱ መንግሥታት ጋር በርካታ ሀገራዊ ኃላፊነቶችን መወጣት ችለዋል። በተያያዥነትም በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ጽ/ቤት ሰበካዊ ጉዳዮችን ከሐዋርያዊ እና የልማት ጽ/ቤት ጋር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
በካርዲናልነት ማዕረጋቸው በቅድስት መንበር በበርካታ ካርዲናሎች ጉባኤዎች በመሳተፍ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳሳትን አማክረዋል። ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው “ለሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን በአብሮነት፤ በተሳትፎ እና ተልዕኮ” በሚል መሪ ቃል 16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል ለ3 ዓመታት ተሳትፈዋል።
ብፁዕነታቸው ለቅድስት መንበር ለቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ያቀረቡት የጡረታ እረፍት ጥያቄ ባሳለፍነው ግንቦት ወር 2018 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህም መሠረት ለተተኪያቸው ለብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ የአዲስ አበባ ሊቀጳጳስ ኃላፊነታቸውን በማስረከብ በካርዲናልነታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛን ማማከራቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል። በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም በሐዋርያዊ አገልግሎት ድጋፋቸውን በጳጳሳት ጉባኤ፣ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት እና በልዩ ልዩ ሁኔታዎች በሚቀርብላቸው ግብዣ መሠረት አገልግሎታቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።
ክህነት ከተቀቡ ሀምሳ ዓመታትን በዛሬው ዕለት የሚያክብሩት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የአገልግሎት ዘመናቸው በፈተና እና በተለያዩ ከባድ ሁኔታዎች የተሞላ ቢሆንም በጥበብ እና በእምነት ጽናት በክህነት፣ በጳጳስነት፣ በካርዲናልነት ሲያገለግሉ ለብዙዎች ጥበብ የተሞላበት የታላቅ መሪ እና አባት ተምሳሌት ሆነዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊክ የጳጳሳት ጉባኤ ለብፁዕ አባታችን የመልካም ምኞቱን እያስተላለፈ ቀሪ ዘመናቸውን እግዚአብሔር አምላክ ዕድሜና ጤና እንዲሰጣቸው ይመኛል። “በጥበቃሽ ሥር“ ብለው እመቤታችን ድንግል ማርያምን በአገልግሎታቸው ዘመን እነደተማጠኗት ሁሉ አሁንም በቀሪ ዘመናቸው ታማልዳችው ዘንድ እንጸልይላቸው።
ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ሆይ ለምንልን!
ብፁዕ አባ ገብረሚካኤል ሆይ ለምንልን !
