የብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ቀነኒ አጭር የሕይወት ታሪክ

“ሀምሳ ዓመታት የክህነት አገልግሎት፤ የድቁና ትጋት ተምሳሌት!”
ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ቀነኒ ከአባታቸው ቀነኒ ደራራ እና ከእናታቸው ወለተሰንበት አጋ ሕዳር 16 ቀን 1936 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ክፍለ ሀገር ከአዲስ አበባ 73 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሜጫ በሮዶ መንደር ተወለዱ። በአቅራቢያቸው በምትገኘው አስተርእዮ ማርያም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ሲሆን በሕፃንነታቸው ወደ ደብረዘይት በመሄድ የመሠረተ ትምህርት እስከ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አጠናቀቁ። በክረምት እረፍት ጌዜ ወደአዲስ አበባ መጥተው በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ምሥጢረ ቁርባንን ተቀበሉ፡፡
በወቅቱ በተከሰተው የመንግሥቱ ንዋይ እና ግርማሜ ንዋይ የመንግስት ግልበጣ ግርግር ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ሄዱ። በአዲስ አበባ በመጡበት ወቅት የጠዋት ቅዳሴን አዘውትረው ያስቀድሱ የነበሩት ልጅ ጸጋዬ ለክህነት ጥሪ መንገዳቸውን የጀመሩት በዚህ ወቅት መሆኑን ያስታውሳሉ። በወቅቱ የቤተጳጳስ አስተዳዳሪ የነበሩት ክቡር አባ ዘካሪያስ ዮሐንስ የዘርዓ ክህነት ትምህርት እንዲማሩ ባቀረቡላቸው ግብዣ በመቀበል የሀገረስብከቱ ጳጳስ የነበሩት የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኃይለማርያም ካሕሳይ ጋር በመማከር በ1954 ዓ.ም. አጣጥ ሉርድ ማርያም በሚገኘው ዘርዓ ክህነት የአዳሪ ቤት ትምህርታቸውን ጀመሩ። በዚህም መሠረት ስምንተኛ ክፍልን በአጣጥ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት፣ 9ኛ ክፍል በአዲስ አበባ ካቴድራል ዘርዓ ክህነት ት/ቤት፣ ከ10ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በወልመራ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት በመማር ጨርሰዋል። በዚህ ጊዜ ክቡር አባ ዘካሪያስ የክህነት ትምህርት እንዲማሩ በወቅቱ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ አሥራተማሪያም የምሩ ጥያቄ በማቅረብ በሕዳር 1960 ዓ.ም. የፍልስፍናና ነገረ መለኮት ትምህርታቸውን ለመከታተል በጣሊያን ሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጅ በቅድስት መንበር ኡርባኒያ ዪኒቨርስቲ እንዲማሩ ፍቃድ በመጠየቅ ወደ ሮም እንዲላኩ ተደረገ። ዩኒቨርስቲ 3 ዓመት የፍልስፍና እና 3 ዓመት የነገረ መለኮት ትምህርታቸው ካጠናቀቁ በኋላ ለ2 ዓመታት የሐዋርያዊ ነገረመለኮት ትምህርት ላይ በልዩ መልኩ በማተኮር ተጨማሪ ትምህርት በቅድስት መንበር በላተራን ዩኒቨርስቲ በማጥናት ከ8 ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ። አጠቃላይ የክህነት ትምህርት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ በወቅቱ የአዲስ አበባ ረዳት ጳጳስ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ጻድዋ ሰኔ 6 ቀን 1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልደተ ማርያም ካቴድራል ማዕረገ ክህነት ተቀበሉ።
በአገልግሎት ዘመናቸው በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ለውጥ ካመጡ ጠንካራ ካህናት መካከል ግንባር ቀደም የሆኑት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ የድቁና አገልግሎታቸውን የጀመሩት በተጠሩበት ቦታ ሁሉ በመገኘት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ሲሆን ማዕረገ ክህነት ከተቀበሉ በኋላ በሊቀጳጳሱ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት ረዳት ጳጳሱን በማገዝ እና ወጣቶችን በመከታተል አገልግሎታቸውን ጀመሩ።
ከሰኔ ወር 1968 ዓ.ም እስከ 1991 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሲሆን ከብዙዎቹ በጥቂቱ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል።
- ከ1968 ዓ.ም እስከ 1991 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ካርዲናል ጳውሎስ ጻድዋ እንደራሴ
- ከ 1968 ዓ.ም እስከ 1991 ዓ.ም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የቦርድ አባል፣ የቦርድ ፕሬዝደንት እና የኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
- ስብከተ ወንጌል ለማስፋፋት ለዘርዓ ክህነት እና ለዘርዓ ምንኩስና ለሚዘጋጁ ወጣት ተማሪዎች በየሰበካቸው እና በየገዳማቸው በመገኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሰጥተዋል
- ለምዕመናን፣ ለመንፈሳዊ ማህበራት፣ እና ለካቴኪስቶች በየሀገረስብከቱ በመዘዋወር ቁምስናቸውን በዕውቀት እና በጥበብ እንዲመሩ ለማስቻል ሥልጠናዎችን ሰጥተዋል
- ለወጣቶች በነበራቸው ልዩ የአገልግሎት ፍላጎት ለካቶሊካውያን ወጣቶች በየቁምስናው በመዘዋወር መንፈሳዊ ትምህርትን በመስጠት በአገልግሎት ተሳታፊነታቸውን ለማጠናከር በማህበር እና በቁምስና እንዲደራጁ በማድረግ አሰልጥነዋል
- በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ድንጋጌ መሰረት የመጀመሪያውን የምዕመናን ምክር ቤት በ1972 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ቀጥሎም በ1973 ዓ.ም. በብሔራዊ ጽ/ቤት ደረጃ መስርተዋል
የአባ ጸጋዬ የአገልግሎት ዘመን በመቀጠል በአብያተ ክርስቲያናት መተባበር ጉባኤ ካቶሊካዊት ቤተክርቲያንን በመወከል መስራች አባል በመሆን የኮሚቴው ጸኃፊ ሆነው አገልግለዋል። ጉባኤው የሦስት ቤተ ዕምነቶችን ማለትም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የሉተራን ቤተክርስቲያን በጋራ በመሆን ያቋቋሙት ለስብዓዊ አገልግሎት የመተባበርን ዓላማ የያዘ ሲሆን በ1977ዓ.ም. በተከሰተው የድርቅ አደጋ ጥምር የተራድዖ ህብረትን (Joint Relief Partnership, JRP) በማቋቋም በCRS እና LWF በተሰኙ የማህበራዊ ልማት ተቋማት ድጋፍ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በተለይም በአማራ ክልል በወሎ አካባቢ የነፍስ አድን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ከፍተኛውን የመሪነት ሚና ተጫውተዋል። ይህንንም ህብረት በማጠናከር ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት አባል እንዲሆኑ በማድረግ Organization for Social Services, OSSA የተባለውን ተቋም አቋቋሙ። ብፁዕነታቸው ተቋሙን በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን በወቅቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ተመዝግቦ በኤች አይ ቪ ኤድስ የተጠቁ ሰዎች ላይ በማተኮር የቅድመ ጥንቃቄ፣ የመድኃኒት ማከፋፈል እና ስለቫይረሱ ሰፊ ስልጠና በመስጠት ለሀገር ባለውለታ የሆነ ተቋም መሪ ሆነው አገልግለዋል።
ክቡር አባ ጸጋዬ ከ1990 እስከ 1991 ዓ.ም. የብፁዕ አቡነ ብርሃነኢየሱስ እንደራሴ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው በየካቲት ወር 1991 ዓ.ም. በብፁዕነታቸው ፍቃድ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ጠቅላይ ፀሐፊ እንዲሆኑ ተሹመው ለዘጠኝ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በቆይታቸውም የጠቅላይ ጽ/ቤቱን አሁናዊ አወቃቀር ማለትም የሐዋርያዊ እና የልማት ጽ/ቤት ቅርጽ በማስያዝ አመርቂ ለውጥ ማምጣት ችለዋል። ይህም አወቃቀር በተገቢው መልክ እንዲፈጸም የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ኃላፊነቶች በግልጽ በማደራጀት አገልግሎቱን በሁሉም ሀገረስብከቶች እንዲስፋፋ አድርገዋል። በዚህም መሠረት በወቅቱ በነበሩት በሁሉም ሀገረስብከቶች በተመሳሳይ መልኩ በጳጳሳቱ አመራር ሥር የሚተዳደሩ የሐዋርያዊ ጽ/ቤቶች እና የማህበራዊ ልማት አስተባባሪ ጽ/ቤቶች እንዲቋቋም አድርገዋል። በጠቅላይ ጽ/ቤት በነበራቸው የአገልግሎት ዘመን ከሚታወቁበት እና በታሪክ ከሚታወሱበት አንዱ ቤተክርስቲያኒቷ በራሷ የሰው ኃይል የስብከተ ወንጌል ተልዕኮን እንድትወጣ እና ለዚህም የሚውል በገቢ ማስገኛ አማራጮች እና ንብረት በማፍራት ተቋማት ራሳቸውን ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽዎ አበርክተዋል። ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የገቢ ምንጮችን በመፍጠር በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት (CRS) ያለበትን ሕንጻ በማሠራት እና የጠቅላይ ጽ/ቤት ሕንጻውን በማስተካከል የጸሎት ቤት፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የንግድ ሱቆችን መጨመርና የገቢ ምንጭ መጨመር እንዲችል አድርገዋል።
የጠቅላይ ጸሐፊነት አገልግሎታቸውን በማጠናቀቅ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ የቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ፕሮጀክት ዳይሬክተር በመሆን ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም የነቀምት ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቴዎ ጡረታ በወጡበት ጊዜ በጳጳሱ እና በሰበካው ካህናት ጥያቄ መሰረት የነበረውን ክፍተት በመሙላት ለሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ድጋፍ አድርገዋል።

ሕዳር 1 ቀን 2006 ዓ.ም በቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ለሶዶ ሀገረስብከት እረኛ ይሆኑ ዘንድ ተሰየሙ። በሕዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሶዶ ሀገርስብከት በቅድስት ሥላሴ ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና መላው የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ በተገኙበት አንብሮተ እድ “ሁሉ በእርሱ ሆነ” ዮሐ 1፡3 የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል የጵጵስናቸው መሪ ቃል በማድረግ ማዕረገ ጵጵስና ተቀበሉ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ልዩ አርአያ በማድረግ የሚመሩት ብፁዕነታቸው “ሐዋርያው ሲመክር ራስ ወደ ሆነው ክርስቶስ እንደግ (ኤፌ4፡15) በማለት ለእኛ ለአገልጋዮች ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንዳለብን ያሳየናል፡፡ የኛ የእድገት ጉዞ ይሄ ነው፣ ሙሉ ወራሾች ሆኖ መገኘት ነው” ሁልጊዜም መመሪያቸው በማድረግ ለክርስቲያኖች ክርስቶስን ለማውረስ ከምዕመናን፣ ከወጣቶች፣ ከካቴኪስቶች እና ከካህናት ጋር በመሆን በጽናት አገልግለዋል።
በሶዶ ሀገረስብከት በጵጵስና አገልግሎታቸው ሰበካው ራሱን የሚችልበትን አማራጮችን ቅድሚያ በመስጠት የጀመሩ ሲሆን በዚህ ሂደትም የቤተክርስቲያን ባለቤት መሆን የሚችሉ፣ በእምነት የጠነከሩ እና የታጠቁ ክርስቲያኖችን ማፍራት ችለዋል። ይህም ሂደት ፈተና የሞላበት ቢሆንም ቁምስናዎች በምዕመናን ቁጥር፣ በእምነት ጥንካሬ እና በገንዘብ አቅም በጠንካራ ምዕመናንና ካታኪስቶች ማጠናከር እና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ቁምስናዎች ምዕመናን ከቆሞሳት ጋር በህብረት ቤተ ጸሎቶችን በራሳቸው እንዲያንጹ ማድረግ፣ የካህናት መኖሪያ በሌለባቸው ቦታዎች ቤቶችን መገንባት፤ ቤተ ጸሎት የነበሩትን ራሳቸውን ችለው ቁምስና እንዲሆኑ ማድረግ፤ አንዳንድ ከቤተ ጳጳስ ብቻ ይጠበቁ የነበሩ ወጪዎችን መሸፈን፤ ለቤተ ጳጳስ የአሥራት ገንዘብ በማዋጣት መደገፍ እንዲሁም የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን መፍጠርና የገቢ አስተዳደር መተዳደሪያ መመሪያዎችን ማውጣት ከሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ዕድሜአቸው ለጡረታ በደረሰ ጊዜ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና መሠረት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ባቀረቡት የጡረታ እረፍት ጥያቄ እስከ 80 ዓመታቸው ድረስ በማገልገል ሕዳር 2015 ዓ.ም. ጥያቄአቸው ተቀባይነት አግኝቷል። ብፁዕነታቸው የሀገረስብከቱን የማስተዳደር ኃላፊነት ቢያስረክቡም በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ እና በተለያዩ ቦታዎች እጅግ ጥልቅ የሆነውን ምክራቸውን በመለገስ አገልግሎታቸውን በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሥር በመሆን እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ቀጥለዋል።
የትጉህ አገልጋይ ተምሳሌት የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ቀነኒ ምዕመናን ክርስቶስን በመምሰል በቁርጠኝነት በእርሱ ሕይወት ለተጠሩለት ዓላማ እንዲኖሩ የዘወትር ምክራቸው ነው። ወጣቶች ማንነታቸውን እና የተከፈለላቸውን የደም ዋጋ በማስተዋል ልዕልናቸውን እንዲያውቁ በተለያዩ ጊዜያት ጥሪ በማቅረብ ይታወቃሉ። የክርስቲያን አገልግሎት ዓይነት አንዱ ለሆነው እና ለፍጡራን መነሻ ለሆነው ታላቅ ምሥጢር ቤተሰብ ለሚመሠርቱ ባልና ሚስት አንድነታቸው ወደ ተግባር የሚገባው ቤተሰብ ከመሠረቱ በኋላ በመሆኑ በትኩረት እና በአስተውሎት ክርስቶስን በሕይወታቸው እየገለጡ መኖር አለባቸው በማለት አባታዊ ምክራቸውን ዘወትር ይለግሳሉ።
ብፁዕነታቸው፤ በባሕሪያቸው ረጋ ያሉ፣ አስተዋይ፣ በትዕግስት አድማጭ፣ ሁሉን ተቀባይ እና እጅግ ደግ ናቸው፡፡ በብዙ ካቶሊካዊያን እና የካቶሊክ እምነት ተከታይ ያልሆኑ የሰው ልጆችን በመልካም ባሕርያቸው መሳብ ችለዋል፡፡ በልጅነታቸው ከተገናኙት ክቡር አባ ዘካሪያስ ዮሐንስ በድንገት ዘርዓ ክህነት እንዲቀላቀሉ ጥሪ የቀረበላቸው ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ቀነኒ በእግዚአብሔር ጸጋ እና በትጋት አሁን ላሉበት የሀምሳ ዓመታት የክህነት አገልግሎት ደረጃ ለመድረስ በቅተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊክ የጳጳሳት ጉባኤ ለብፁዕ አባታችን የመልካም ምኞቱን እያስተላለፈ ቀሪ ዘመናቸውን እግዚአብሔር አምላክ ዕድሜና ጤና እንዲሰጣቸው ይመኛል።
