በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሴቶች ገዳማውያን ህብረት (ACWET) ሆለታ ወደሚገኘው የአቡነ ብሩክ ቅድስት ሥላሴ የሴቶች ገዳም መንፈሳዊ ንግደት አድረጉ

የቅዱስ ፍራንቼስኮስን ህልፈተ ህይወት 800ኛ አመትን በማሰብ እና የእህትማማች ህብረትን ለማጠናከር የተካሄደው ይህ መንፈሳዊ ንግደት መነሻውን ከአዲስ አበባ በማድረግ በርካታ ሴቶች ገዳማውያትን በማሳተፍ ወደ ሆለታ ጉዞውን አድርጓል። ጉዟቸውን ጃንሜዳ አካባቢ ከሚገኝው የገዳማት ጽ/ቤት በጸሎት የጀመሩት ገዳማውያቱ ከአዲስ አበባ 38 ኪሎ ሚትር ርቀት ላይ ሆለታ በሚገኘው በእማሆይ ሀረገወይን መስራችነት ወደተቋቋመው የአቡነ ብሩክ የሴቶች ገዳም አቅንቷል።
ጉዟቸው በጸሎት እና በተለያዩ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች የታጀበ ሲሆን በዚህ ቁጥር ደረጃ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ፕሮግራም መሆኑ ተገልጿል። ንግደቱ ከ22 በላይ የሚሆኑ ገዳማትን በመወከል ከ60 በላይ የሚሆኑ ገዳማውያትን አሳትፏል።
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የሴቶች ገዳማውያት ህብረት (ACWECA) አካል የሆነው ይህ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ሴቶች ገዳማውያን ህብረት መንፈሳዊ ንግደታቸውን የቅዱስ ፍራንቼስኮስ ህልፈተ ህይወት 800ኛ አመትን በማሰብ መደርጉን የማህበሩ ፕሬዝደንት የሆኑት ሲስተር ጌጤነሽ ወልደአምላክ ገልጸዋል። በመርሃግብሩም የቅዱስ ፍራንቼስኮስ ህይወት እና መንፈሳዊነት በተመለከተ ክቡር አባ ሀይለገብርኤል መለቁ የካፑቺን ገዳም ካህን አስተምረዋል።
በንግደቱ የተሳፉት ገዳማውያት በበኩላቸው በመርሃግብሩ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በመንፈሳዊ ንግደቱ የቅዱስ ፍራንቼስኮስን ህይወት የበለጠ መረዳት እና አገልግሎቱን በማሰብ መጸለያቸውን ገልጸዋል።

ከንግደቱ ባሻገር በኢትዮጵያ የምስራቅ ሥርዓት መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመውን የአቡነ ብሩክ ቅድስት ሥላሴ የሴቶች ገዳም በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ገዳማውያቱ በአቡነ ብሩክ ገዳም ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ በማካሄድ መርሃግብሩን አጠናቅቀዋል።
