የምሰራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ (አመስያ) የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ውይይት በአዲስ አበባ ተደረገ

የ“ውዳሴ ላንተ” የቤተክርስቲያን ሰነድ ትግበራን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የግምገማ ውይይት በምሰራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤ አዘጋጅነት እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ትብብር በአዲስ አብባ ሀገረስብከት የኮንሶላታ አባቶች ገዳም ተካሂዷል። በጉባኤው በዘርፉ ዝግጅት ያላቸው የአመስያ አባል ሀገራት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን “ውዳሴ ላንተ” ”Laudato Si” የተሰኘው የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ የተዘጋጀ ሐዋርያዊ ማነቃቂያ ላይ በቀጠናው እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች ላይ በዝርዝር መወያየት ተችሏል።
ጉባኤው ከሚያዝያ 6 – 8 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን በሐምሌ ወር ለሚደረገው 21ኛው የአመስያ ጳጳሳት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት አካል መሆኑን በኪንያ ናይሮቢ የሚገኘው የማህበራዊ ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ክቡር አባ ጳውሎስ ገልጸዋል። “ይህ የውይይት መድረክ የአባል አገራት በአየር ንብረት ለውጥ እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በተግባር ላይ ያሉ ስራዎችን ለመገምገም እንዲሁም ለወደፊት የተያዙ ዕቅዶች ላይ ለመወያየት እድል የሚሰጥ ነበር” ብለዋል። በተጨማሪም በአ.አ 2022 ላይ በታንዛኒያ ጳጳሳቱ የ“ውዳሴ ላንተ” ሰነድ ትግበራን በተመለከተ ያስቀመጧቸውን ሰባት አቅጫዎች ላይ ባለፉት አራት አመታት የተደረሰበትን መግምገም ተችሏል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና ሊቀጳጳስ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በመገኘት ተወካዮችን ተቀብለው አወያይተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ልዑካኑን ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ በኢትዮጵያ ያሉትን የተፈጥሮ ስጦታዎች እና የኢትዮጵያውያንን ከተፈጥሮ ጋር ቁርኝት ገልጸዋል። ተፈጥሮን እና ምድርን መንከባከብ ክርስቲያናዊ ኃላፊነት መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ጉባኤው በሀግራችን መካሄዱ እንዲሁም ወደፊት የዚህ አይነት ጉባኤዎች ለማዘጋጀት መመረጧ የሀገራችን ዜጎችም ሆነ መንግስት በአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት መሆኑን አንስተዋል።

በጉባኤውም በዘርፉ ላይ አገልግሎት በመስጠት አመርቂ ውጤት እና ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኙ ተቋማት እና ማህበራት ልምድ ልውውጥ ተደርጓል። በቀጣይም ከፍተኛ አገልግሎት በመስጥት ላይ ያሉ እንደ ላውዳቶ ሲ አለምአቀፍ እንቅስቃሴ እና የመሳሰሉትካቶሊካዊ ተቋማት ጋር በቀጠናው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ አሳቻይ አማራጮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ ካሳለፍነው አመት ካዘጋጀችው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አንስቶ ወደፊት የምታዘጋጃቸው ታላላቅ አለምአቀፍ መድረኮች ላይ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያላትን አስተምሮ የሚያንጸባርቁ ተቋማት ጋር በመተባበር በተለይም የችግሩ ተጋላጭ እንደመሆኗ መጠን በአንድነት እና በተባበረ አቅም ድምጽን ማሰማት ተገቢ እንደሆነ የጉባኤው ተሳታፊዎች አንስተዋል።
