ካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያ 27ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን የማህበራዊ ልማቶች የሚመራው ጽ/ቤት ካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያ 27ኛ መደበኛ ጉባኤውን በጠቅላይ ጽ/ቤት አካሄደ።

ጉባኤው በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የመክፈቻ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን እ.ኤ.አ የ2025 አመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት፣ የኦዲት ሪፖርት እና የእ.ኤ.አ 2026 ዕቅድ፣ እንዲሁም የተቋሙን የአርማ  እና የሥያሜ ለውጥ ዋና አጀንዳዎች በማድርግ ውይይት አድርጓል።  

ብፁዕ ካርዲናል ለጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በቀድሞ ስያሜው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊ ልማት ጽ/ቤት አዲስ ስያሜ እና አርማ ማዘጋጀቱን በማሳወቅ “ካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያን” ይፋ አድርገዋል። በመቀጠልም ተቋሙ እ.ኤ.አ የ2025 አመት የተከናወኑ አበይት ተግባራትን በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በሴቶች እድገት፣ በውሀ ሥራዎች፣ በስደት እና ከስደት ተመላሾች እና በሌሎች ዘርፈ ብዙ የአገልግሎት መስኮች የተከናወኑ ተግባራትን አንስተዋል።

ብፁዕነታቸው “ዛሬ ቤተክርስቲያናችን ቤተሰብን ለማብቃት፣ የኑሮ መተዳደሪያን ለመደገፍ እና የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት የምታደርገው ጥረት እና ድጋፍ ለነገው ሰብዓዊ ክብር መሠረት እንዲሆን ለማድረግ ያስችለናል” ብለዋል።

የካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ የጽ/ቤቱን አመታዊ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ቤተክርስቲያኗ ባሳለፍነው ዓመት 207 ፕሮጀክቶችን በመተግበር ከ10 ቢሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር አማካይነት 6.5 ሚሊዮን ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ደጋፍ ማድረጓን ገልጸዋል። ይህንንም ያስቻለው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከአስራ ሦስቱ ሀገረስብከቶች እና ከሀምሳ ሰባት የገዳማት ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባኤው በመቀጠል የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አማራጮች ጋር ለመተግበር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ የተወያየ ሲሆን በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ አስተዳደራዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ተወያይቷል።

ጉባኤው ብፁዓን ጳጳሳት፣ የጳጳሳት እንደራሴዎች፣ የቦርድ አባላት፣ የገዳማት አለቆች፣ የአጋር ድርጅት ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተወካዮች እና የጠቅላይ ጽ/ቤት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና ሠራተኞች በተገኙበት ተካሂዷል።  


Leave a Reply

“በነፃ የተቀበላችሁት በነፃ ስጡ”

ማቴዎስ 10፡7-15

አስተንትኖ፡ የሚስዮናዊ ደቀመዝሙርነት ራስን መቻልን፣ መተማመንን እና ልግስናን ይጠይቃል። የተላክነው ለጥቅም ሳይሆን የምስራቹን ቃል ለማወጅና ለመባረክ ነው።

    The Catholic Bishops Conference of Ethiopia (CBCE)
  • Wawel Street, Besides of Catholic Cathedral, Piassa
  • CBCE@cbce-gs.org
  • scpr@eccsdco.org
  • +251-11-1550300