የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሎቭር ዲ ኦሪየንት ተቋም ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናዋን አቀረበች

እ.ኤ.እ 1856 L’Œuvre d’Orient በመባል የተመሰረተው ሎቭሬ ዲኦሪየንት የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋም የተመሰረተበትን 170ኛ ዓመት አከበረ። በፈረንሳይ ፓሪስ ኖትረ ዳም ካቴድራል በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ሎረንት ኡልሪች በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዲካስቴሪ ኃላፊ የተመራ ሲሆን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ የጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ፕሬዚደንት እና ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ በቦታው ተገኝተዋል።
ላለፉት 170 ዓመታት ማህበሩ ሰብአዊ እርዳታን፣ የሐዋርያዊ ድጋፍን እና በርካታ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የቆየ ሲሆን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ የተቋሙን 170ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሉቨር ዲ ኦሪየንት በኢትዮጵያ ላሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የአካባቢው ማህበረሰብ ሲያደርግ ለቆየው ድጋፍ አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ሎቭሬ ዲ ኦሪየንት በኢትዮጵያ ከሚሰጣቸው ሐዋርያዊ አገልግሎቶች መካከል ለትምህርት ዘርፍ እና የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመርዳት ልዩ አስተዋጽዖ ማበርከታቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በተለያዩ የህንጸት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን በሐዋርያዊው ዘርፍ አቅም ለማጎልበት እገዛ ማድረጋቸው ተነስቷል።
ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ፕሪፌክት እና የፓሪስ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ በተገኙበት መርሃግብር ባስተላለፉት መልዕክት ሎቭር ዲ ኦሪየንት በመላው ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በማህበራዊ ድጋፍ፣ ላይ ላበረከቱት ሰፊ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው “ሎቭሬ ዲኦሪየንት ለምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት እና ለኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማህበረሰባችንን በቀጥታ እና በROACO አማካይነት ረድቷል፣ እናም ለሁሉም ታላቅ ምስጋናችንን እናቀርባለን” ብለዋል።
በበአሉ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሉቭር ዲ ኦሪየንት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እንዲሁም ከሊሎች እምነት ተቋማት ጋር በመትባበር ሰፊውን ህዝብ እንዴት ያለማቋረጥ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
የሎቭሬ ዲኦሪንት ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቡነ ሁየስ ደ ዎይልሞንት እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጋር በቅርበት የሰሩ ለጋሾችን፣ የፕሮጀክት ኃላፊዎችን እና ተወካዮችን በሕይወት ላሉም ሆነ ለሞቱ አመስግነዋል።
ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ በተጨማሪም የተቋሙ እርዳታ ካቶሊካውያንን ብቻ ሳይሆን የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን፣ የወንጌላዊ ማህበረሰቦችን እና የሙስሊም ማህበረሰቦችን ጭምር እንደጠቀመ አፅንዖት ሰጥተው፣ ሎቭሬ ዲኦሪንት በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን አንድነት እና ማህበራዊ ትስስር በማጎልበት ረገድ ያለውን ሚና አፅንዖት ሰጥተዋል።
