ለወንድም ግሪጎሪ እና ለእህት ካትሪን መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ተካሄደ።

ባሳላፍነው ሳምንት ከዚህ አለም ድካም ላረፉት ለክቡር ለወንድም ግሪጎሪ እና ለእህት ካትሪን መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ተካሄደ። በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ወንድም ግሪጎሪ በምክትል ጠቅላይ ጸኃፊነት እንዲሁም ክብርት እህት ካትሪን በማህበራዊ ተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል መስራች እና ኃላፊ ሆነው ላገለገሉት ገዳማውያን መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በጠቅላይ ጽ/ቤት የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ተደርጓል።
በተጨማሪም መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የጽዮን ማርያም ቁምስና ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ እና ካህናት በተገኙበት ለእህት ካትሪን የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ተከናውኗል። በዕለቱም የእህት ካትሪን ምድራዊ ህይወትን በመዘከር የፍቅር ሥራ ልጆች ገዳም፣ የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽኃፊ እና የማህበረ ልዑካን በኢትዮጵያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ።

ሲስተር ካትሪን ለማህበረሰቡ ካበረከቱት ሰብዓዊ አገልግሎት ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የማህበራዊ ተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል በመመስረት እና ተልዕኮውን ለማስቀጠል ሰራተኞችን በማሰልጠን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሰፊ ማህበረሰብ የስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ በዘርፉ ዘላቂ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በክፍሉም ከነበራቸው አስተዋጽዖ የፍቅርና ሰላም ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ሀገረስብከት በመረከብ በጳጳሳት ጉባኤ ደረጃ የመጀመሪያውን ወርሃዊ ጋዜጣ ማስጀመራቸው፣ የሬድዮ እና የድምጽ መቅጃ ስቱዲዮ ማስገንባታቸው፣ የካቶሊክ የስልክ እና አድራሻ መዝገብ ማስጀመራቸው፣ እና የቤተክርስቲያኗን አገልግሎቶች በተንቀሳቃሽ ምስል እንዲቀመጡ ለማስቻል መሳሪያዎችን በማሟላት እና ባለሙያዎችን በስልጠናዎች በማብቃት የሰጡት አገልግሎት ከብዙዎቹ በጥቂቱ ይገለጻሉ። ጡረታ እስከወጡበት ግዜ ድረስ በዚህ ቢሮ ውስጥ ያለመታከት በኃላፊነት አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት በህይወት ላጣናቸው እነዚህ ታላላቅ ገዳማውያን በተለይም በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በኩል ስላበረከቱት አስተዋጽዖ እና ስለህይወታቸው እያመሰገንን ለነፍሳቸው ዘለዓለማዊ እረፍትን እንጸልያለን።
