ለብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ ታደሰ የ”ፓሊየም” አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት በቫቲካን ተከናወነ

ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ ታደሰ ገብረስላሴ የኮምቦኒ ማሕበር አባል ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሜትሮፓሊታን ሊቀ ጳጳስ፣ የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዩኒቬርሲቲ ቻንስለር ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ለብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ ታደሰ “የፓሊየም” አሰጣጥ መንፈሳዊ ስነ-ሥርዓት ለማካሄድ በተለምዶ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ በነበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው የጤና እክል አጋጥሟቸው በሮም በሚገኘው አጎስቲኖ ጄሜሊ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ማክሰኞ ጥቅምት 03/2019 ዓ.ም በመግባታቸው የተነሳ በወቅቱ ቅዱስነታቸው ከሕመማቸው አገግመው ከሆስፒታል መቼ እንደሚወጡ እርግጠኛ ስላልነበረ፣ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተወከሉትና፣ በቫቲካን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ዋና ጸኃፊ በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ በኩል በቫቲካን በሚገኘው በጳጳሳዊው የኢትዮጵያ ኮሌጅ በጥቅምት 17/2019 ዓ.ም የ”ፓሊየም” አሰጣጥ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግላን፣ ምዕመናን እና ተጋባዢ እንግዶች በተገኙበት መከናወኑ ተገልጿል።
“ፓሊየም” የላቲን ቃል ሲሆን ከነጭ የበግ ሱፍ የሚሠራ እና በሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳሳት ካባ ትክሻ ዙሪያ ላይ የሚደረግ ከነጭ የበግ ሱፍ የሚሰራ ነው። “ፓሊየም” (pallium) የተሠራው፣ በስም ትርጉሙ፣ በክርስቲያናዊ ምሳሌዎች እና በጥንታዊ የሮማውያን የባሕል ወጎች የተሞላ ጥልቅ ትርጉም ባለው መልኩ፣ በቅድስት አኜስ አመታዊ በዓል ማለትም እ.አ.አ በጥር 21 ቀን ከተባረኩ ሁለት በጎች ሱፍ ነው። (“አኔስ” ከላቲን ቋንቋ ጋር ባለው ግንኙነት (“በግ”) የሚለውን ትርጓሜ የሚሰጠን ሲሆን፣ በሕዝባዊ የቃላት አመጣጥ ትርጓሜ (folk etymology) አማካኝነት፣ ይህ ስም “በግ” ከሚለው የላቲን ቃል “አኙስ” (agnus) ጋር በቅርበት ይያያዛል። በዚህም ምክንያት፣ በክርስቲያናዊ ስነ-ጥበብ ውስጥ ቅድስት አኜስ (Saint Agnes) ንጽህናን እና መስዋዕትነትን በሚወክል በግ ታጅባ ትገለጻለች)።

“ፓሊየም” ለሮማ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳሳት እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በልዩ ሁኔታ ለሚመርጧቸው ጳጳሳት ብቻ የሚሰጥ፣ በትክሻ ዙሪያ በሚገኝው ካባ ላይ የሚደረግ የክብር እና የመንፈሳዊ ስልጣን ምልክት ነው። “ፓሊየም” የተቀበለ አንድ የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ በቤተ ክርስቲያን ወግ፣ አሰራር እና በሕገ ቀኖና ደንብ ላይ ተመስርቶ በአገሩ ውስጥ ለተሾሙ አዳዲስ ጳጳሳት የጵጵስና ማዕረግ መስጠት የምያስችለውን መንፈሳዊ ሥልጣን የምያጎናጽፈው ሲሆን በእዚህም ተግባሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ከእያንዳንዱ የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ አገር ጳጳሳት ጋር መንፈሳዊ አንድነታቸውን ጠብቀው ይሄዱ ዘንድ ያስችላቸዋል።
መነሻው፡ቃሉ የመጣው ከላቲን “ፓሊየም” (የሮማውያን ፈላስፎች ካባ) ከተሰኘው ነው። በጥንታዊ የክርስትና ጥበብ፣ ኢየሱስ እና ሐዋርያት የሐይማኖት “መምህራን” መሆናቸውን የምያሳይ መንፈሳዊ ምልክት ሆኖ አገልግሏል።
የሥርዓተ አምልኮው ትርጉም
ሥነ-ሥርዓቱ በርካታ መሠረታዊ ተምሳሌታዊ ተግባሮችን ያካትታል፥
“ፓሊየም” በሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳሱ ካባ ትክሻ ዙሪያ ላይ ጣል የሚደረግ እጄታ የለሽ “ስቶላ” መሰል ከበግ ሱፍ የተሠራ ሲሆን ትርጓሜውም የመልካሙ እረኛ እና ጠፍቶ የተገኘው በግ ምሳሌን ያመለክታል (ሉቃስ 15 ይመልከቱ) “ፓሊየም” ጠፍቶ የተገኘውን በግ በትክሻው ላይ አድርጎ የተሸከመውን መልካሙን እረኛ ያመለክታል፣ “ፓሊየም”ን በትክሻው ዙሪያ ላይ በሚገኘው ካባ ላይ ያጠለቀው አንድ የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ኃጢአተኛውን ወይም የጠፋውን በግ የሚሸከመውን መልካሙን እረኛ ክርስቶስን የምያመልክት ሲሆን የእረኝነት ተግባሩን እና ነፍሳትን የመንከባከብ ሸክምን ወይም መስዋዕትነትን ይወክላል።
የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ያለው ትስስር፥ “ፓሊየም” የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ከሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ጋር የምያስተሳስር፣ አንድነታቸውን እና ሕብረታቸውን የሚገልጽ የቤተ ክርስቲያን አንድነትን እና ሕብረትን የሚያሳይ ምልክት ነው። ይህም የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ግዛት ውስጥ ያለው የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ሥልጣን ከሮም ቤተክርስቲያን ጋር ሙሉ በሙሉ አንድነት እንዳለው ያሳያል።
የክርስቶስ ቁስሎች፡- በላቲን ቋንቋ “ፓሊየም” 5 ሴ.ሜ ያህል ስፋት ያለው “እስቶላ” መሰል ከነጭ ከበግ ሱፍ የተሰራ ሲሆን በላዩ ላይ በጥቁር ክር የተፈተሉ መስቀሎች ይገኛሉ፣ እነዚህ ጥቁር መስቀሎች የክርስቶስን ሕማማት ቁስሎች ያስታውሳሉ፣ ይህም ይህንን “ፓሊየም” በትክሻው ላይ በሚገኘው ካባ ዙሪያ ላይ የምያጠልቀው የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለመስዋዕትነት እና እምነቱን ለመመስከር ያለውን ፈቃደኛነት እና ቁርጠኝነት ያስታውሳሉ።
ሶስት የብረት ሚስማሮች፦ በ”ፓሊየም” ላይ ከመስቀሎቹ መካከል ሦስቱ ትናንሽ የብረት ወይም የወርቅ ሚስማሮች ተቸንክሮው የሚገኙበት ጥበብ ይገኛል። እነዚህም ክርስቶስን በመስቀል ላይ ለማቆየት ጥቅም ላይ የዋሉትን ሚስማሮች ወይም እርሱ በመከራው ወቅት የተወጋባቸውን እሾህ ይወክላሉ።
ጥቁር ጫፍ ያላቸው ተንጠልጣይ ክፍሎች፤ ከፊትና ከኋላ በኩል ወደ ታች የሚወርዱት ሁለቱ ቁመት ያላቸው ቁርጥራጮች፣ ጥቁር የሐር ወይም የጨርቅ ጫፎች አሏቸው። እነዚህ የበግ ሰኮናን የሚመስሉ ሲሆን፣ ልብሱ እንዳይርገበገብ ወይም በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቆይ ለማድረግ በውስጣቸው ትናንሽ የእርሳስ ክብደቶች ይዘዋል።
የ”Y” ቅርጽ እና የቀንበር መልክት፣ በአንገት ዙሪያ ያለው ቀለበት እና ወደ ታች የሚወርዱት ማሰሪያዎች የ”Y” ቅርጽ ይፈጥራሉ። ይህ የክርስቶስን ኃላፊነት የሚወክል፣ ከባድ ቢሆንም ረጋ ያለ የሆነውን ቀንበር፤ እንዲሁም ሊቀ ጳጳሱ ለመንጋው እንደ አከርካሪ አጥንት (እንደ ዋና ደጋፊ) ያለውን ሚና ያመለክታል፣ (እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የተደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ 11፡28-30)።
የአንድነትና የሥልጣን መገለጫ፤ ‘ፓሊየም’ (pallium) የተባለውን ምልክት በቀጥታ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እጅ ወይም ከተወካያቸው መቀበል (ይህም እንደ ልማዱ በቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ አመታዊ በዓል፣ ማለትም እ.አ.አ ሰኔ 29 ቀን ይከናወናል፣ እንደ አስፈላጊነቱም በተለየ ቀን ሊሰጥ ይችላል)፣ ከቅድስት መንበር ጋር ያለን አንድነት እንዲሁም የተጋራ የሐዋርያዊ (የእረኝነት) ሥልጣን መኖሩን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነው።
ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ ታደሰ፣ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ በመሆን የእረኝነት ኃላፊነታቸውን በታማኝነት ቤተክርስቲያንን በመምራት ሲያገለግሉ የነበሩት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ተክተው በጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት የልደታ ማርያም ካቴድራል በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ የሊቀ ጳጳሳት መንበሩን መረከባቸው የሚታወስ ሲሆን ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ተስፋሥላሴ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሜትሮፓሊታን ሊቀ ጳጳስ፣ የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዩኒቬርሲቲ ቻንስለር ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፣ የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለብጹዕ አባታችን መልካም የእረኝነት አገልግሎት ይሆን ዘንድ መልካም ምኞቱን እና ትሁት ጸሎቱን ያረጋግጣል።

ምንጭ፡ የቫቲካን ዜና
