የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሰብዓዊ ክብር እና ሕይወት በተመለከተ የተላለፈ ሐዋርያዊ ጥሪ

“ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና”. (ማቴ 5:7)
ለፖለቲካ መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ሚዲያዎች እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ
የተከበራችሁ ወንድሞች እና እህቶች
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት በመላው አለም ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወቅታዊ ሁኔታች እንዳሳሰበን ለመግለጽ እንፈልጋለን። በአገራችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች አገራቸውን ለቀው የሚወጡት ለአገራቸው ፍቅር በማጣት ሳይሆን፣ የተሻለ የሥራ ዕድል እና የኑሮ ሁኔታ በመፈለግ ነው። ተነሳሽነታቸው እጅግ ሊከበር የሚገባው እና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነው፤ ይህም ህይወታቸውን ለማሻሻል፣ ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እና በመጨረሻም ለአገራቸው እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው። ነገር ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ስደተኞቻችን የሚያስፈልጋቸውን ሰብዓዊ ክብር ከማግኘት ይልቅ በመዋቅራዊ ብዝበዛ፣ በፍርሃት፣ በገለልተኝነት እና በከባድ ተጋላጭነት ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ። ሁኔታቸው ምንም ያህል ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም፣ ቅዱስ የሆነው ሰብአዊ ክብራቸው ግን በድንበር፣ በሕጋዊ ሁኔታ ወይም በኢኮኖሚ ስርዓት ችላ ሊባል ወይም ሊጠፋ አይችልም።
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፤ “በኢኮኖሚ የበለጸጉ መንግስታት፣ ሰዎች በትውልድ አገራቸው ጸጥታንና ለመተዳድሪያ የሚሆን ገቢ በማጣታቸው ወደ አገራቸው ሲገቡ ተቀብለው የተቻላቸውን እርዳታ መስጠት አለባቸው” (CCC 2241)። ይህ ትምህርት ስደተኞች እንደ ውጭ ወይም እንደሸክም መታየት እንደሌለባቸው ይልቁንም እንደ ወንድምና እህት ሰብዓዊ ክብራቸው ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚገባ ያስተምረናል።
ይሁን እንጂ፣ ብዙ ስደተኞች በስደት ጉዟቸው ወቅት ከባድ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል፤ በእጅጉም ይሰቃያሉ። እኛም ከዚህ በታች የተገለጹትን ቁልፍ የስደት መዳረሻዎች እና ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚያጋጥሟቸውን ተያያዥ ችግሮች ተመልክተናል።
1)አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች፡-
ሀ. ሳውዲ አረቢያ፡- በሳውዲ አረቢያ መንግሥት የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አሉ። የኢትዮጵያ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በተለያዩ የሚዲያ ዘገባዎች በሰማነው መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ በተፈረደው የሞት ፍርድ ያለንን ስጋት፣ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን። የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት ለዜጎቻችን ሁሉ ርህራሄ እና ምሕረት እንዲያደርጉ ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት እንዲጠብቁ እንጠይቃለን።
ለ. የመን፡– በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ የመን ለመግባት ወይም ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመጓዝ በቀይ ባህር፣ በጅቡቲ ወይም በኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል ያልፋሉ። የመን ብዙውን ጊዜ ወደ ሌሎች የባህረ ሰላጤ አገሮች እንደ መጓጓዣ መንገድ ትጠቀማለች፤ ሆኖም ግን፣ ብዙ ስደተኞች በመንገድ ላይ ከፍተኛ ሥቃይ ይደርስባቸዋል፣ ዓመፅ፣ በደል እና ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ይደርስባቸዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በጉዞው አደገኛ ባህሪ እና በሚገጥሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ።
ሐ. ሊባኖስ፡– በሊባኖስ የሚገኙ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአገሪቱ ውስጥ ባለው ግጭትና አለመረጋጋት ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። በዚህም ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ትውልድ አገራቸው በሰላም ለመመለስና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ይፈልጋሉ።
መ. የባህረ ሰላጤ አገሮች፡– በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአሌሪካ በእስራኤል እና በኢራን መሃከል በተፈጠረው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት በጭንቅ ውስጥ ይገኛሉ።
2) የደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሌላ መዳረሻ ናት። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ወደአስቡበት ሳይደርሱ በጉዞ ላይ እያሉ እስራት ይገጥማቸዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ መድረሻቸው የሚደርሱ ሰዎች በፍርሃትና ውስጥ በምኖር ላይ ናቸው። በሚደርሱን ዘገባዎች መሰረት በደቡብ አፍሪካውያን የውጭ ዜጎች ጥላቻ የተነሳ በዓመፅ፣ እና በግድያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ክቡር ሕይወታቸው እየጠፋ ነው።
3) የሱዳን – ሊቢያ – የአውሮፓ መንገድ፡ ይህ መንገድ ለረጅም ጊዜ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በብዛት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ሲሆን፣ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ስደተኞች ከፍተኛ ስቃይ እና ህልፈተ ህይወት አስከትሏል። ብዙዎች አስቸጋሪ እና አደገኛ የሆነውን የበረሃ መንገድ በኢሰብአዊ ሁኔታዎች ሲያቋርጡ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአሁኑ ጊዜ በሱዳን እየተካሄደ ያለው ግጭት ይህንን ጉዞ የበለጠ አደገኛ አድርጎታል። ሊቢያ የሚደርሱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እስር፣ ዝርፊያ፣ የጉልበት ብዝበዛ እና ከባድ በደል ይደርስባቸዋል። አንዳንዶቹ በክርስትና እምነታቸው ምክንያት ስደት ደርሶባቸዋል እና ህይወታቸውን አጥተዋል። በአደገኛ ጀልባዎች የሜዲትራኒያንን ባህር ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች ሲሰምጡ፤ ብዙዎቹ በሚያሳዝን ሁኔታ ህይወታቸውን ያጣሉ፣ ጥቂቶች ብቻ ወደ ላምፔዱዛ ዳርቻ መድረስ ችለዋል። ላምፔዱዛ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ በአንድ ወቅት በባህር ላይ ለሞቱት ሰዎች መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለስደተኞች ያላትን አንድነት፣ ርህራሄ እና ለስደተኞች ድምጽ የመሆን ተልዕኮ ለማስቀጠል ደሴቲቱን በቅርቡ እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።
ይህ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስቃይ ከቁጥርም በላይ ውድ እና የተከበረ ህይወት ያላቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው በእንባ፣ በመስዋዕትነት እና በተስፋ የሸኟቸው ልጆች ናቸው። ብዙ ጊዜ ግን እነዚህ ስደተኞች በብዝበዛ፣ በፍርሃት፣ በደል፣ በመገለል እና ለጥቃት በመጋለጥ አላስፈላጊ ስርዓቶች ውስጥ ይወድቃሉ። ብዙዎች ለማሰብ አዳጋች በሆኑ ሁኔታዎችን ውስጥ በህይወት ለመቆየት ይታገላሉ።
በክርስቲያያዊ የበጎ አድራጎት እና በዓለም አቀፍ የወንድማማችነት መንፈስ፣ ለሳውዲ አረቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ማናቸውም የታቀዱ ግድያዎች እንዲቆሙ እና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምሕረትን እንዲያደርጉ ልመና እናቀርባለን። ምህረት ፍትህን አያዳክምም። ምህረት ፍትህን ከፍ በማድረግ ተስፋ ለቆረጡ ተስፋን ይሰጣል።
ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የሚያባብሱትን ጥልቅ ምክንያቶች ከመሰረቱ ለማስወገድ ይተባበር ዘንድ ዕድል የሚሰጥ ሊሆን ይገባል። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፣ የከባቢ አየር ሁኔታ መቃወስ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በዓለም ዙሪያ አደገኛ የፍልሰት መንገዶችን እንዲከተሉ እንደሚያስገድዳቸው አስተውለናል። እነዚህን ዋና ዋና ምክንያቶች ችላ የሚል ዓለም የፍልሰት ቀውስን መፍታት አይችልም። በእርግጥም፣ የሰብዓዊነታችን እና የሥልጣኔ መለኪያ በዙሪያችን ያሉ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች በምናሳሳየው እንክብካቤ ላይ የተመሠረተ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት፣ ውይይት፣ ምሕረትና ጥበብ ተስፋ መቁረጥንና ሞትን እንዲያሸንፉ አጥብቀን መጸለያችንን እንቀጥላለን። እነዚህን ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ሁሉንም ውሳኔ ሰጪዎች ለሁሉ ቻይ በሆነው የእግዚአብሔርን አምላክ ምህረት እና እገዛ ያገኙ ዘንድ እንጸልያለን።
የኢትዮጵያ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ
አዲስ አበባ
10/09/2018
