ከሐምሌ 30 – ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲካሄድ የቆየው 60ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት አመታዊ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ

በየአመቱ ሁለት መደበኛ ጉባኤዎቹን የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ላላፉት ሶስት ቀናት 60ኛውን ጉባኤ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የአጽናኝቷ ማርያም ገዳም አካሂዷል።
60ኛ መደበኛ ጉባኤ የጉባኤውን ተተኪ ፕሬዝደንት በመምረጥ የተጀመረ ሲሆን ላለፉት 28 ዓመታት የጳጳሳት ጉባኤውን በፕሬዝደንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስን ስላበረከቱት እጅግ የላቀ አስተዋጽዖ በማመስገን ተጠናቅቋል።
ብፁዓን ጳጳሳቱ ለጉባኤያቸው የያዟቸው መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የትግበራ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።
እንዲሁም በሲኖዶሳዊት ቤተክርስቲያን የተቀመጡ የትግበራ አማራጮች ላይ በመወያየት በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፍ ተጨማሪ ባለሙያዎችን በማሰማራት ከወጣቶች እና ከምዕመናን ጋር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የቤተክርስቲያኗን ተቋማት የሥራ ሂደት እና አስተዳደር የገመገሙት ብፁዓን ጳጳሳቱ ነባራዊ ተግዳሮቶችን ይቀርፋሉ ያሏቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል።
