የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ለ2018 ዓ.ም. የፍልሰተ ማርያም ጾም መግቢያ ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት
«የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም አንድነት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።» (2 ቆሮንቶስ 13፥14)
በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 15 ቀን ድረስ የምንጾመውና የምንጸልየው የፍልሰታ ለማርያም ጾምና ሱባኤ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እጅግ ታላቅና ቅዱስ የጸጋ ጊዜ ነው። ይህ ወቅት መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምናድስበት፣ ወደ አምላካችን በንሰሐ የምንቀርብበት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት የምንማጸንበት እንዲሁም በተለየ ሁኔታ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት የሰላም ጉድለት ችግር ፈውስንና ሰላምን ከመለኮት የምንለምንበት የተባረከ ጊዜ ነው።
የፍልሰታ ለማርያም ጾም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምድር ሕይወቷን አጠናቃ ወደ ሰማያዊ በክብር የመወሰዷንና ታላቅ ምስጢር የምናስብበት ወቅት ነው። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረው፣ እመቤታችን የጸጋ ሁሉ ሙላት ያደረባትና የሰላም ንጉሥ የሆነውን መድኃኔዓለምን በማኅፀኗ የተሸከመች የእግዚአብሔር እናት በመሆኗ ወደ ዘላለም ክብር ተሸጋግራለች።
ይህ ቅዱስ የጾም ወቅት አእምሯችንን ከጥል፣ ከቂም እንዲሁም ከዓለማዊ ጭንቀቶች ሁሉ አርቀን ከእግዚአብሔርና ከራሳችን ጋር የምንታረቅበት ታላቅ የንሰሐና የጽሞና ጊዜ ነው። እንዲሁም፣ የእመቤታችን ወደ ሰማይ መውጣት በምድር ላይ በመከራና በስጋት ውስጥ ለምንኖር ሁላችንም የጽናት፣ የትንሣኤና የዘላለም ሰላም ተስፋችን ማረጋገጫ ነው።
ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ መልካም ነገር እየሆነላት እንደሆነ እናምናለን። እንዲሁም እየተደረገ ያለውን የሰላም፣ የእርቅ እና የውይይት ጥረት እያበረታታን አሁንም ግን በብዙ አቅጣጫዎች ሀገራችን ብርቱ የሰላም ጥማት፣ የማኅበራዊ ስብራትና የሕዝቦች መከራ ውስጥ ትገኛለች። የጦርነት፣ የስደተኞች እንባ፣ የኑሮ ውድነትና የሞራል ውድቀት ወንድማማቾችን እና እህትማማቾችን እርስ በእርስ ከፋፍሏል። ይህ የፍልሰታ ጾም ለአገራችን ታላቅ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ፋይዳ አለው። ጌታችን ኢየሱስ «ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ» (ዮሐንስ 14፥27) እንዳለው፣ ያለ እግዚአብሔር ሰላም ሰብአዊ ጥረታችን ብቻውን አገርን ማዳን አይችልም። ስለዚህ ይህ የሱባኤና የምህለላ ወቅት የቂም ግንቦችን አፍርሰን፣ በትህትና እርቅንና ሰላምን የምንገነባበት ወሳኝ ወቅት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ «በክርስቶስ ሆነን፦ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናችኋለን» (2 ቆሮንቶስ 5፥20) እንዳለው፣ የእመቤታችንን አማላጅነት በብቃት የምንማጸነው እርስ በእርሳችን ስንዋደድና የሰውን ልጅ ሕይወት ክብር ስንጠብቅ ነው። በመሆኑም የጥላቻና የልዩነት ንግግሮችን አስወግደን በእውነተኛ ወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ ልንቆም ይገባል።
እመቤታችን በመስቀሉ ሥር ቆማ የልጇን መከራ ስታይ ልቧ በሰይፍ ተወግቶ ነበር (ሉቃስ 2፥35)። ዛሬም የሚያለቅሱ እናቶችን፣ ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆችንና የተፈናቀሉትን ሕመም ታውቃለች። ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ «እናትህ እነኋት» (ዮሐንስ 19፥27) ብሎ እንደሰጠን፣ እኛም በዚህ ጾም የእመቤታችንን እናታዊ ጥበቃ በመጠየቅ የተጎዱትን ልንደግፍ ይገባል።
በዚህ ቅዱስ የፍልሰታ ሱባኤ ወቅት ካቶሊካውያን ምዕመናንና ክርስቲያኖች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ስለ አገራችን ሰላም አጥብቀው ሊጸልዩና ሊጾሙ ይገባል። ጾም በምግብ ብቻ ሳይሆን በአንደበትም በልብም ጭምር ነው። ቅዱስ ዳዊት «ነፍሴን በጾም አስጨነቅኋት» (መዝሙር 69፥10) እንዳለው፣ በጾማችን ወቅት በቃላቶቻችን ሰላምን እንጂ ጥላቻን አንዝራ። በመቁጠሪያ ጸሎታችን ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም፣ እንዲሁም መሪዎቻችን እግዚአብሔር አስተዋይነትን እንዲያበዛላቸው አጥብቀን እንጸልይ።
በሁለተኛ ደረጃ፣ የምሕረትና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በትጋት መሥራት ይኖርብናል። ነቢዩ ኢሳይያስ «እኔ የምወደው ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ… የተራበውን ታበላ ዘንድ፥ የተፈናቀሉትን ደካሞች ወደ ቤትህ ታስገባ ዘንድ አይደለምን?» (ኢሳይያስ 58፥6-7) ይላል። አሁን ባለንበት የመከራ ወቅት በጦርነትና በችግር ምክንያት የተፈናቀሉትን፣ የተራቡትንና አረጋውያንን መደገፍ የጾማችን ዋና ፍሬ ሊሆን ይገባል።
በመጨረሻም፣ የመነጋገርና የምሕረት ባህልን ማሳደግ ያስፈልጋል። በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታና በማኅበረሰብ ደረጃ ያሉትን ቅሬታዎች በእውነትና በፍትህ መንፈስ ሆነን ለይቅርታ መዘጋጀት ይኖርብናል። በቅዱስ መጽሐፍ «ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም ነው፥ እንዴትስ ያማረ ነው!» (መዝሙር 133፥1) ተብሎ እንደተጻፈው፣ ልዩነቶቻችንን በመነጋገርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ እንሁን።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «እነሆኝ የጌታ ባሪያ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ» (ሉቃስ 1፥38) በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የተቀበለችው በትህትናና በሰላም ነው። እኛም ዛሬ የጥላቻና የክፋት መንገድ በፍቅር ተዋግተን በሰላም፣ በይቅርታና በመከባበር መንገድ እንድንመላለስ አደራ እንላለን። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚካሄዱ የተለያዩ ምክክሮች ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ ሁላችንም በጸሎት እንድንተባበር ጥሪያችንን አናቀርባለን።
አምላካችን እግዚአብሔር ጾማችንን፣ ጸሎታችንንና ሱባኤያችንን የተቀደሰ ያድርግልን፤ በውድ አገራችን ኢትዮጵያ ላይ ዘላቂ ሰላሙን እና እርቁን ያውርድልን። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ጥበቃና አማላጅነት ከአገራችንና ከሕዝቦቻችን ጋር ይሁን!
መልካም የፍልሰታ ለማርያም የጾምና የሱባኤ ወቅት ይሁንላችሁ!
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
